solomon asrat solomon asrat

September 17 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 11:17-34
የጌታ እራት

17ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚጐዳ እንጂ ለሚጠቅም ስላልሆነ፣ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ እያመሰገንኋችሁ አይደለም። 18ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ። 19ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው። 20በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤ 21በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል። 22ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።

23እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ 24ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 26ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

27እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል። 28ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤ 29ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣል። 30ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው። 31ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር። 32ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኰነን ነው።

33ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ፣ ማንም የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር ደግሞ በምመጣበት ጊዜ እደነግጋለሁ።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 2:1-13

አድልዎ ማድረግ አይገባም

1ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደመሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። 2የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ 3ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም መቀመጫ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ 4በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን?

5የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? 6እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? 7በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን?

8በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ መልካም እያደረጋችሁ ነው። 9አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤ 10ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቈጠራል። 11“አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደልም” ብሎአልና። ባታመነዝር፣ ነገር ግን ብትገድል፣ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል።

12ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፤ 13ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል።

ወንጌል

ዮሐንስ 1:15-37
15
ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። 16ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ 17ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። 18ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ

19አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር።

20ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ በግልጽ መሰከረ።

21እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት።

እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ።

እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት።

እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ።

22በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት።

23ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።

24ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ 25“ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት።

26ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።”

28ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።

የእግዚአብሔር በግ

29ዮሐንስ በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ 30‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ 31እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።”

32ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ 33በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ 34አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ።”

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

35በማግሥቱ፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ 36ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ።

37ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

Read More
solomon asrat solomon asrat

September 12 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 6:1-10

1ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን መጠን፣ የተቀበላችሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን። 2እርሱ፣

“በትክክለኛው ሰዓት ሰማሁህ፤

በመዳንም ቀን ረዳሁህ” ይላልና።

እነሆ፤ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤

የመዳንም ቀን አሁን ነው።

ጳውሎስ የተቀበለው መከራ

3አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። 4ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ 5በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣ 6በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ 7በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣ 8በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ፣ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ 9የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ 10ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 5:8-12
8
እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል። 9ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ ያለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል።

10ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። 11በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።

12ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ ያለዚያ ይፈረድባችኋል።

ወንጌል

ማቴዎስ 11:1-19

መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላከው ጥያቄ

1ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ።

2ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣ 3“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።

4ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤ 6በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

7የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ? 8ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ። 9ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው። 10እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤

“ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣

ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

11እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤ 13ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና። 14እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው። 15ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

16“ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤

17“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤

አልጨፈራችሁም፤

ሙሾ አወረድንላችሁ፤

አላለቀሳችሁም’

18ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”

Read More
solomon asrat solomon asrat

September 10 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 1:1-9

1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስ፣ ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፤

2በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ተቀድሰው፣ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤

3ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ምስጋና

4በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 5ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በእርሱ በልጽጋችኋል፤ 6ስለ ክርስቶስ የመሰከር ንላችሁም በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። 7ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጒጒት በመጠባበቅ ላይ ሳላችሁ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም። 8በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትገኙ እርሱ እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንቶ ይጠብቃችኋል። 9ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

2 ጴጥሮስ 3:10-18
10
የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል።

11እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ 12ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። 13እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።

14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። 15የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ 16እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

17እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። 18ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ሉቃስ 17:11-37
ከለምጽ የነጹ ዐሥር ሰዎች

11ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኵል ዐለፈ፤ 12ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ 13በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት።

14እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ።

15ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ 16በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።

17ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? 18ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?”። 19ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት

20ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ 21ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።”

22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። 23ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ 24ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። 25ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል።

26“በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። 27ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።

28“በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ 29ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።

30“የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። 31በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። 32የሎጥን ሚስት አስታውሱ። 33ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል። 34እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። 35ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። 36ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ አብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”

37እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት።

እርሱም፣ “ጥንብ ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።

Read More
solomon asrat solomon asrat

September 3 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብራውያን 7:5-14
5
ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዓሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዛል። 6ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዓሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው። 7ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም። 8በአንድ በኩል ዓሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል። 9እንዲያውም ዓሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዓሥራት ከፍሎአል ማለት ይቻላል፤ 10ምክንያቱም መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር።

ኢየሱስ እንደ መልከጼዴቅ

11ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? 12የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። 13ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። 14ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 2:14-26
እምነትና ሥራ

14ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? 15አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ 16ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል? 17እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።

18ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ይላል።

እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። 19አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ።

20አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? 21አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? 22በዚህም እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ። 23“አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። 24እንግዲህ በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።

25እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 26ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው።

ወንጌል

ሉቃስ 12:16-26
16
ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ 17ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።

18“እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’

20“እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው።

21“ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”

አትጨነቁ

22ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ 23ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 25ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው? 26እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ?

Read More
solomon asrat solomon asrat

August 27 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 7:25-40
25
ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ። 26አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል። 27አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ። 28ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወዳለሁ።

29ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ። 30የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤ 31በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደ ማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና።

32እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሰኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ 33ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ 34በዚህም ልቡ ተከፍሎአል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች። 35ይህንም የምለው ለእናንተ የሚበጃችሁን ነገር በማሰብ እንጂ ላስጨንቃችሁ አይደለም፤ ዐላማዬም ልባችሁ ሳይከፈል በጌታ ጸንታችሁ በአግባብ እንድትኖሩ ነው።

36አንድ ሰው ያጫትን ድንግል በአግባቡ ካልያዘ፣ እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ሊያገባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና ይጋቡ። 37ነገር ግን በዚህ ጒዳይ ልቡን አረጋግቶ፣ ሳይና ወጥ፣ ራሱንም በመግዛት ድንግሊቱን ላለማግባት የወሰነ ሰው መልካም አድርጎአል። 38ስለዚህ ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ።

39አንዲት ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ከእርሱ ጋር የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን፣ የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት። 40እንደ እኔ ከሆነ ግን ሳታገባ እንዲሁ ብትኖር ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።

ሁለተኛ ምንባብ

2 ዮሐንስ 1:1-13

1ሽማግሌው፤

በእውነት ለምወዳት እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤ 2በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፣ 3ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።

4ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው። 6ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።

7ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 8እናንተም የደከማች ሁበትን ዋጋ እንዳታጡ፣ ነገር ግን ሙሉ ሽልማት እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው። 10ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ 11የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና።

12የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በወረቀትና በቀለም እንዲሆን አልፈልግም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

13የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

ወንጌል

ማቴዎስ 25:1-13

የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ

1“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። 2ከእነርሱም አምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ አምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ 3ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። 4አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። 5ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።

6“እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።

7“በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። 8ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው።

9“አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው።

10“ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።

11“ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ።

12“እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።

13“እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።

Read More
solomon asrat solomon asrat

August 20 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 6:12-23
12
ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።

የጽድቅ ባሮች

15እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን? በጭራሽ አይገባም! 16ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምት ታዘዙት ለእርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደሆናችሁ አታውቁምን? 17ነገር ግን የኀጢአት ባሮች የነበራችሁ ቢሆንም፣ ለተሰጣችሁለት ትምህርት በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ 18ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ፣ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።

19በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኵሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ። 20የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ። 21አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው። 22አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። 23የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 4:1-17
ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ

1በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ምኞታችሁ አይደለምን? 2ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም። 3ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና።

4አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? 6ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣

“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤

ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል”

ያለው ስለዚህ ነው።

7እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።

11ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?

ስለ ነገ መመካት

13እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። 14ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። 15ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል።

ወንጌል

ዮሐንስ 7:32-52
32
ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጒምጒ ምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው።

33ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋር የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ 34ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።”

35አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? 36‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤’ ደግሞም፣ ‘እኔ ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”

37የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ 38በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” 39ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀ በሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።

40ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ።

41ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ።

ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? 42መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” 43ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ 44አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም።

የአይሁድ መሪዎች አለማመን

45በመጨረሻም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ፣ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም ጠባቂዎቹን፣ “ለምን አላመጣችሁትም?” አሏቸው።

46ጠባቂዎቹም፣ “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ።

47ፈሪሳውያንም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተም ተታላችኋል ማለት ነው? 48ለመሆኑ ከባለሥልጣኖችና ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለ? 49ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።”

50ከዚህ ቀደም ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከእነርሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፤ 51“ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?”

52እነርሱም፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምር፤ ትደርስበታለህ” ብለው መለሱለት።

Read More
solomon asrat solomon asrat

August 13 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 8:1-13
ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ

1ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም። 3እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።

4እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፤ 6ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።

7ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። 8ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።

9ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ። 10አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን? 11ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው። 12በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 4:1-5
ለእግዚአብሔር መኖር

1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።

ወንጌል

ማቴዎስ 12:38-50
ማረጋገጫ ምልክት ስለ መሻት

38ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት።

39እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። 40ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። 41የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። 42በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

43“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። 44ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። 45ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

የኢየሱስ እናትና ወንድሞች

46ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። 47አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።

48ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። 49በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ 50በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”

Read More
solomon asrat solomon asrat

August 6 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ቲቶ 3:1-15
በጎ የሆነውን ማድረግ

1ሰዎች ለገዦችና ለባለ ሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው። 2እንዲሁም በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ አስገንዝባቸው።

3ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኝነት እንኖር ነበር። 4ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ 5ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ 6ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ 7ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው። 8ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።

9ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና። 10መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ። 11እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ።

የመጨረሻ ምክር

12አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ እንደ ላክሁ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጵልዮን ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ላሳልፍ ወስኛለሁ። 13ሕግ ዐዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን በጒዟቸው ለመርዳት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ አሟላላቸው። 14ከእኛ ወገን ለሆኑት ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙና ኑሮአቸውም ፍሬ የሌለው እንዳይሆን ለመልካም ሥራ መትጋትን ይማሩ ዘንድ ይገባቸዋል።

15ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ከእምነት የተነሣ ለሚወዱን ሰላምታ አቅርቡልን።

ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 4:6-11
6
ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።

7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ማርቆስ 6:47-56
47
በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። 48ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። 49ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሎአቸው ጮኹ፤ 50ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። 51እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሮአቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤ 52የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር።

53በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ። 54ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ 55ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። 56በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።

Read More
solomon asrat solomon asrat

July 30 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 9:1-15
1
ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቶአል። 3እንግዲህ በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ወንድሞችን ልኬአለሁ። 4ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ያን ያህል በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን። 5ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።

በልግስና መስጠት

6ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል። 7እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል። 8ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ 9ይህም፣

“በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤

ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል”

ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

10ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። 11ሁል ጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።

12ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጒድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው። 13የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ስለ ታዘዛችሁና ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ስላሳያችሁት ልግስና ሰዎች ተፈትኖ ስላለፈው አገልግሎታችሁ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ 14ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ይናፍቋችኋል። 15በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 3:15-22
15
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።

ወንጌል

ማቴዎስ 24:36-51
የሚመጣበት ቀንና ሰዓት አለመታወቁ

36“ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። 37ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ 38ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ 39እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። 40በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። 41ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።

42“እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። 43ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። 44የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።

45“በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ እንግዲህ ማነው? 46ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤ 47እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48ነገር ግን ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ 49ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ 51ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።


Read More
solomon asrat solomon asrat

July 23 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 10:1-18

ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ

1እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ። 2ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በዓለማዊ መንገድ እንደምንኖር አድርገው በሚቈጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር ቈርጫለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ዐይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3የምንኖረው በዚህ ዓለም ቢሆንም፣ የምንዋጋው በዚህ ዓለም ስልት አይደለም። 4ደግሞም የምንዋጋበት የጦር መሣሪያ የዚህ ዓለም መሣሪያ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደምሰስ የሚችል መለኮታዊ ኀይል ያለው ነው። 5በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን። 6መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ አለ መታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት ተዘጋጅተናል።

7እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል። 8ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበል ነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና። 9በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። 10አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ። 11እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።

12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመ ዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያነጻ ጽሩ አስተዋዮች አይደሉም። 13እኛ ግን ከመጠን በላይ አንመካም፤ የምንመካው እግዚአብሔር በመደበልንና እስከ እናንተም እንኳ በሚደርሰው የአገልግሎታችን ወሰን ነው። 14የክርስቶስን ወንጌል ይዘን ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ፣ ከተመደበልን የአገልግሎት ወሰን አላለፍንም። 15ደግሞም ሌሎች በደከሙበት ሥራ ከመጠን በላይ በመመካት ከተመደበልን ወሰን አናልፍም፤ ይልቁንም እምነታችሁ እያደገ በሄደ ቍጥር በእናንተ ዘንድ የተመደበልን አገልግሎት እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን። 16ስለዚህ በሌላው ሰው ክልል አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ሳንመካ፣ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር ወንጌልን መስበክ እንችላለን። 17ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤ 18ምክንያቱም ጌታ ራሱ የሚያመሰግነው እንጂ፣ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ተቀባይነት አይኖረውም።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 3:1-8

አንደበትን መግታት

1ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። 2ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።

3ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። 4ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። 5እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ 6ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች።

7ማናቸውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። 8ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት።

ወንጌል

ማቴዎስ 8:1-34

የለምጻሙ መንጻት

1ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።

3ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 4ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው።

የመቶ አለቃው እምነት

5ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ 6“ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቶአል” አለው።

7ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።

8የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ 9እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።”

10ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ 11እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ 12መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

13ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።

ኢየሱስ ብዙዎችን መፈወሱ

14ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጎራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታማ ተኝታ አገኛት። 15እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው።

16በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። 17በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤

“እርሱ ደዌያችንን ተቀበለ፤

ሕመማችንንም ተሸከመ።”

የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ውሳኔ ይጠይቃል

18ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። 19በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

20ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።

21ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።

22ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

23ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። 24ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። 25ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።

26ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ።

27ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።

ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች

28ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። 29እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።

30ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 31አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። 32ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። 33የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። 34እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት።

Read More
solomon asrat solomon asrat

July 16 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብራውያን 6:7-20
7
ዘወትር በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። 8ነገር ግን እሾህና አሜኬላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቦአል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው።

9ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋር የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። 10እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። 11የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 12በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።

የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ርግጠኛነት

13እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ 14እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” 15አብርሃምም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ የተሰጠውን ተስፋ አገኘ።

16ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላውም የተባለውን ነገር ስለሚያጸና፣ በመካከላቸው የተነሣው ክርክር ሁሉ ይወገዳል። 17እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው፤ 18እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጎአል። 19እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። 20ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 3:8-14
መልካም በማድረግ መከራን መቀበል

8በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ። 9ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። 10ስለዚህ፣

“ሕይወትን የሚወድ፣

መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣

ምላሱን ከክፉ፣

ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።

11ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤

ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤

12ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤

ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤

የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”

13መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? 14ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።

ወንጌል

ማቴዎስ 13:1-30
የዘሪው ምሳሌ

1በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር አጠገብ ተቀመጠ። 2ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቶአቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። 3ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። 6ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። 7አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን አንቆ አስቀረው፤ 8ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”።

10ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት።

11እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤

“እያዩ ስለማያዩ፣

እየሰሙ ስለማይሰሙ ወይም ስለማያስተውሉ ነው።

14እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤

“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤

ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።

15የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤

ጆሮአቸውም አይሰማም፤

እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣

በጆሮአችው ሰምተው፣

በልባቸውም አስተውለው፣

ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’

16የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን የተባረኩ ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።

18“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ 19የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። 20በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። 21ነገር ግን ሥር መስደድ ባለመቻሉ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። 22በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራውን ሰው ይመስላል። 23በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

የእንክርዳዱ ምሳሌ

24ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። 25ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም አብሮ ብቅ አለ።

27“የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት።

28“እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው።

“አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።

29“እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ 30ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”

Read More
solomon asrat solomon asrat

July 9 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ጢሞቴዎስ 4:1-22
1
በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤ 2ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም። 3ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። 4እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። 5አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

6እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል። 7መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። 8ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

የጳውሎስ ማሳሰቢያ

9በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ 10ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዶአልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ 11ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና። 12ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። 13ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ።

14አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጒዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል። 15መልእክታችንን እጅግ ተቃውሞአልና፣ አንተም ከእርሱ ተጠንቀቅ።

16በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው። 17ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ። 18ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

የስንብት ሰላምታ

19ለጵርስቅላና ለአቂላ፣ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። 20ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቶአል፤ ጥሮፊሞስም ስለ ታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። 21ከክረምት በፊት እዚህ ለመምጣት የተቻለህን አድርግ። ኤውግሎስና ጱዴስ እንዲሁም ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22ጌታ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

ሁለተኛ ምንባብ

2 ጴጥሮስ 1:12-18
የቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢት

12ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸ ኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። 13በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ 14ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ 15እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ።

16ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ እኮ የእርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፣ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም፤ 17ምክንያቱም ከግርማዊው ክብር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሎአል፤ 18እኛም ከእርሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል።

ወንጌል

ሉቃስ 6:1-19
የሰንበት ጌታ

1በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። 2ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።

3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? 4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኀብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” 5ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

6በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። 7ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። 8ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካካል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

9ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።

10ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። 11ሰዎቹ ግን በቊጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ

12ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። 13ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ 14እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ 15ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፤ 16የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።

የቡራኬና የወዮታ ስብከት

17ኢየሱስም አብሮአቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፣ 18እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ 19ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።

Read More
solomon asrat solomon asrat

July 2 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 10:1-18
ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ

1እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ። 2ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በዓለማዊ መንገድ እንደምንኖር አድርገው በሚቈጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር ቈርጫለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ዐይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3የምንኖረው በዚህ ዓለም ቢሆንም፣ የምንዋጋው በዚህ ዓለም ስልት አይደለም። 4ደግሞም የምንዋጋበት የጦር መሣሪያ የዚህ ዓለም መሣሪያ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደምሰስ የሚችል መለኮታዊ ኀይል ያለው ነው። 5በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን። 6መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ አለ መታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት ተዘጋጅተናል።

7እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል። 8ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበል ነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና። 9በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። 10አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ። 11እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።

12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመ ዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያነጻ ጽሩ አስተዋዮች አይደሉም። 13እኛ ግን ከመጠን በላይ አንመካም፤ የምንመካው እግዚአብሔር በመደበልንና እስከ እናንተም እንኳ በሚደርሰው የአገልግሎታችን ወሰን ነው። 14የክርስቶስን ወንጌል ይዘን ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ፣ ከተመደበልን የአገልግሎት ወሰን አላለፍንም። 15ደግሞም ሌሎች በደከሙበት ሥራ ከመጠን በላይ በመመካት ከተመደበልን ወሰን አናልፍም፤ ይልቁንም እምነታችሁ እያደገ በሄደ ቍጥር በእናንተ ዘንድ የተመደበልን አገልግሎት እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን። 16ስለዚህ በሌላው ሰው ክልል አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ሳንመካ፣ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር ወንጌልን መስበክ እንችላለን። 17ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤ 18ምክንያቱም ጌታ ራሱ የሚያመሰግነው እንጂ፣ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ተቀባይነት አይኖረውም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 5:1-14

ለሽማግሌዎችና ለጎልማሶች የተሰጠ ምክር

1እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ 3እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን። 4የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ።

5ጐልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣

“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤

ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”

6ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።

8ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል። 9በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።

10በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። 11ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።

የስንብት ሰላምታ

12እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በስልዋኖስ አማካይነት ይህንን አጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ።

13ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። 14በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።

በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን።


ወንጌል

ማቴዎስ 16:1-12
ኢየሱስ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ መጠየቁ

1ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት በመሻት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።

2እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ 3ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቶአል፣ ከብዶአልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም። 4ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቶአቸው ሄደ።

የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን እርሾ

5ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። 6ኢየሱስም፣ “ልብ በሉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።

7እነርሱ ግን እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” ተባባሉ።

8ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ እንጀራ ስለ አለመያዛችሁ ለምን ትነጋገራላችሁ? 9አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? 10እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? 11ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” 12በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።

Read More
solomon asrat solomon asrat

June 25 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 5:12-21
ሞት በአዳም፣ ሕይወት በክርስቶስ

12ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። 14ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።

15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! 16ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!

18ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።

20ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ 21ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

3 ዮሐንስ 1:1-15
1
The elder,

To my dear friend Gaius, whom I love in the truth.

2Dear friend, I pray that you may enjoy good health and that all may go well with you, even as your soul is getting along well. 3It gave me great joy when some believers came and testified about your faithfulness to the truth, telling how you continue to walk in it. 4I have no greater joy than to hear that my children are walking in the truth.

5Dear friend, you are faithful in what you are doing for the brothers and sisters, even though they are strangers to you. 6They have told the church about your love. Please send them on their way in a manner that honors God. 7It was for the sake of the Name that they went out, receiving no help from the pagans. 8We ought therefore to show hospitality to such people so that we may work together for the truth.

9I wrote to the church, but Diotrephes, who loves to be first, will not welcome us. 10So when I come, I will call attention to what he is doing, spreading malicious nonsense about us. Not satisfied with that, he even refuses to welcome other believers. He also stops those who want to do so and puts them out of the church.

11Dear friend, do not imitate what is evil but what is good. Anyone who does what is good is from God. Anyone who does what is evil has not seen God. 12Demetrius is well spoken of by everyone—and even by the truth itself. We also speak well of him, and you know that our testimony is true.

13I have much to write you, but I do not want to do so with pen and ink. 14I hope to see you soon, and we will talk face to face.

15Peace to you. The friends here send their greetings. Greet the friends there by name.

ወንጌል

ማቴዎስ 22:1-22
በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ

1ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ 2“መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ 3ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ።

4“እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ።

5“ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። 7ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።

8“ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ 9ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ 10አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።

11“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ 12እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም።

13“ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ 14የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ግብር ስለ መክፈል

15ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። 16ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ 17ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

18ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? 19ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። 20እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።

21እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት።

እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

22ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።

Read More
solomon asrat solomon asrat

June 18 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 14:1-25
የትንቢትና የልሳን ስጦታዎች

1ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። 2በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለ ሚናገር የሚረዳው የለም። 3ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። 4በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። 5ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፣ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።

6እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ? 7እንደ ዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? 8ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ ትርጒም ያለው ቃል ካልወጣ፣ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። 10በዓለም ላይ ብዙ ዐይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለውም ቋንቋ የለም። 11እንግዲህ አንድ ሰው የሚናገረውን ቋንቋ ትርጒሙን ካላወቅሁ፣ ለሚናገረው እንግዳ እሆንበታለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆንብኛል። 12እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት የምትሹ በመሆናችሁ፣ ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ።

13ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። 14በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 15ታዲያ፣ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። 16እንዲህማ ካልሆነ እግዚአብሔርን በመንፈስ በምታመሰግንበት ጊዜ፣ ለነገሩ እንግዳ የሆነ ሰው አንተ የምትናገረውን ካልተረዳ፣ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፣ “አሜን” ሊል ይችላል? 17አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም።

18ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 19ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።

20ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ፤ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ። 21በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤

“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፣

በባዕዳንም አንደበት፣

ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤

ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፤”

ይላል ጌታ።

22ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 23እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፣ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፣ አብደዋል አይሉምን? 24ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሣል፤ በሁሉ ይመረመራል፤ 25በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፣ “እግዚአብሔር በርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 4:1-8
መናፍስትን መርምሩ

1ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 2የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚቀበል መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ 3ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።

4ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል። 5እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ የሚናገሩት እንደ ዓለም ነው፤ ዓለምም ይሰማቸዋል። 6እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።

የእግዚአብሔር ፍቅርና የሰው ፍቅር

7ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። 8የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።

ወንጌል

ዮሐንስ 15:17-27
17
እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት።

ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ

18“ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። 19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። 20‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። 21የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። 22መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። 24ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል። 25ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።

26“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ

Read More
solomon asrat solomon asrat

June 11 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ኤፌሶን 4:1-16
በክርስቶስ አካል ያለ አንድነት

1እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። 2ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። 3በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ 6ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።

7ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። 8ስለዚህም እንዲህ ይላል፤

“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣

ምርኮ ማረከ፤

ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።”

9ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? 10ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። 11አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ 12ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ 13ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው።

14ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። 15ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤ 16ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 2:1-17
1
ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።

3ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። 4“እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ 6ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው። 9በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። 10ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። 11ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

12ልጆች ሆይ፤

ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

13አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

14አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤

ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣

የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣

ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣

ጽፍላችኋለሁ።

ዓለምን አትውደዱ

15ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

ወንጌል

ዮሐንስ 14:1-21
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታ

1“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። 3ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። 4እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”

ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ

5ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።

6ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”

8ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።

9ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። 12እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። 13አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ 14ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።

ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ተስፋ

15“ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። 16እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሮአችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። 18ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። 21የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”

Read More
solomon asrat solomon asrat

June 4 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 15:20-40
20
ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። 21ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። 22ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ 23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። 24ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ 27“ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሎአልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።

29ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? 30እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? 31ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። 32በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤

“ነገ ስለምንሞት፣

እንብላ፣ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው።

33አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” 34ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።

የትንሣኤ አካል

35ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። 36አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። 37የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። 38እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። 40እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 1:1-12
1
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኝነት ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ምርጦች፤ 2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።

ሕያው ስለ ሆነው ተስፋ ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና

3የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ 4እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን። 5እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። 6አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። 7እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንደተረጋገጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። 8እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል፤ 9የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።

10ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ 11በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። 12አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ባበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።

ወንጌል

ዮሐንስ 20:1-18
ኢየሱስ ከሞት ተነሣ

1በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። 2ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

3“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። 5ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። 6ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ 7እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። 8ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ 9ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

10ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ 11ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። 12የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች።

13እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።

እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። 14ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም።

15እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት።

እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው።

16ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት።

እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው።

17ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።

18መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

Read More
solomon asrat solomon asrat

May 28 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 10:1-21
ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። 2ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም። 3ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። 4ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።

5ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። 6ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7“ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። 8ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ 9“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። 10የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። 11መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” 12በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ 13“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”

14ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? 15ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

16ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና። 17እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው። 18ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤

“ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣

ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።”

19ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤

“ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናቸዋለሁ፤

ማስተዋል በሌለው ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ”

20ኢሳይያስም በድፍረት፣

“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤

ላልጠየቁኝ ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል።

21ስለ እስራኤል ግን፣

“ወደማይታዘዝና እሺ ወደማይል ሕዝብ፣

ቀኑን ሙሉ እጄን ዘረጋሁ” ይላል።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 3:15-22
15
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።

ወንጌል

ሉቃስ 24:45-53
45
በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ 47ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”

የኢየሱስ ዕርገት

50ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ 53እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።

Read More
solomon asrat solomon asrat

May 21 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 4:14-25
14
በሕግ የሚኖሩት ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት የማይጠቅም፣ ተስፋም ከንቱ በሆነ ነበር፤ 15ሕግ ቊጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም።

16ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቶአል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የእርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው፤ 17ይህም “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው።

18“ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ። 19እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም። 20ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ 21እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር። 22ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።” 23“ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለእርሱ ብቻ አይደለም፤ 24ነገር ግን እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ ለሚቈጥርልን፣ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው በእርሱ ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው። 25እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።

ሁለተኛ ምንባብ

ራእይ 20:1-15
የሺህ ዓመቱ መንግሥት

1የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው። 3ሺሁ ዓመትም እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።

4ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለእርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግምባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ። 5የቀሩት ሙታን ግን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። 6በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።

የሰይጣን የመጨረሻ ዕጣ

7ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ 8በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፦ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። 9እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው። 10ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።

ሙታን ተፈረደባቸው

11ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። 13ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት። 14ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።

ወንጌል

ዮሐንስ 21:1-14
ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው

1ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ 2ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ 3ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም።

4ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።

5እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው።

እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።

6እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው።

7ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ። 8ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። 9ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ።

10ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው።

11ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። 12ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። 13ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤

ዓሣውንም ሰጣቸው። 14እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።

Read More
solomon asrat solomon asrat

May 14 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 6:1-14
ለኀጢአት መሞት፣ በክርስቶስ ሕያው መሆን

1እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር? 2ከቶ አይሆንም፤ ለኀጢአት ሞተናል፤ ታዲያ እንዴት አድርገን ከእንግዲህ በእርሱ እንኖራለን? 3ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንድንሆን የተጠመቅን፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? 4ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር ተቀብረናል።

5በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን። 6ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ 7ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል።

8ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን። 9ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጒልበት አይኖረውም። 10በሞተ ጊዜ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኀጢአት ሞቶአል፤ ነገር ግን በሕይወት መኖርን ለእግዚአብሔር ይኖራል።

11እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቊጠሩ። 12ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 4:1-11
ለእግዚአብሔር መኖር

1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።

7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ዮሐንስ 21:15-25
ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ቀድሞ ቦታው መለሰው

15በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው።

እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።

16ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው።

እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።

17ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው።

ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። 18እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” 19ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።

20ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። 21ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ።

22ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። 23በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።

24ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።

25ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።


Read More