May 28 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 10:1-21
ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። 2ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም። 3ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። 4ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
5ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። 6ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7“ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። 8ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ 9“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። 10የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። 11መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” 12በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ 13“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
14ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? 15ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
16ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና። 17እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው። 18ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤
“ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣
ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።”
19ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤
“ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናቸዋለሁ፤
ማስተዋል በሌለው ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ”
20ኢሳይያስም በድፍረት፣
“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤
ላልጠየቁኝ ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል።
21ስለ እስራኤል ግን፣
“ወደማይታዘዝና እሺ ወደማይል ሕዝብ፣
ቀኑን ሙሉ እጄን ዘረጋሁ” ይላል።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:15-22
15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ሉቃስ 24:45-53
45በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ 47ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
የኢየሱስ ዕርገት
50ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ 53እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።