September 12 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 6:1-10

1ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን መጠን፣ የተቀበላችሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን። 2እርሱ፣

“በትክክለኛው ሰዓት ሰማሁህ፤

በመዳንም ቀን ረዳሁህ” ይላልና።

እነሆ፤ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤

የመዳንም ቀን አሁን ነው።

ጳውሎስ የተቀበለው መከራ

3አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። 4ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ 5በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣ 6በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ 7በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣ 8በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ፣ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ 9የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ 10ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 5:8-12
8
እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል። 9ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ ያለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል።

10ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። 11በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።

12ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ ያለዚያ ይፈረድባችኋል።

ወንጌል

ማቴዎስ 11:1-19

መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላከው ጥያቄ

1ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ።

2ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣ 3“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።

4ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤ 6በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

7የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ? 8ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ። 9ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው። 10እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤

“ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣

ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

11እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤ 13ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና። 14እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው። 15ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

16“ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤

17“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤

አልጨፈራችሁም፤

ሙሾ አወረድንላችሁ፤

አላለቀሳችሁም’

18ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”

Previous
Previous

September 17 2023

Next
Next

September 10 2023