July 16 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብራውያን 6:7-20
7
ዘወትር በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። 8ነገር ግን እሾህና አሜኬላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቦአል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው።

9ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋር የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። 10እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። 11የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 12በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።

የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ርግጠኛነት

13እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ 14እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” 15አብርሃምም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ የተሰጠውን ተስፋ አገኘ።

16ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላውም የተባለውን ነገር ስለሚያጸና፣ በመካከላቸው የተነሣው ክርክር ሁሉ ይወገዳል። 17እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው፤ 18እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጎአል። 19እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። 20ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 3:8-14
መልካም በማድረግ መከራን መቀበል

8በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ። 9ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። 10ስለዚህ፣

“ሕይወትን የሚወድ፣

መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣

ምላሱን ከክፉ፣

ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።

11ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤

ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤

12ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤

ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤

የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”

13መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? 14ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።

ወንጌል

ማቴዎስ 13:1-30
የዘሪው ምሳሌ

1በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር አጠገብ ተቀመጠ። 2ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቶአቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። 3ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። 6ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። 7አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን አንቆ አስቀረው፤ 8ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”።

10ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት።

11እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤

“እያዩ ስለማያዩ፣

እየሰሙ ስለማይሰሙ ወይም ስለማያስተውሉ ነው።

14እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤

“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤

ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።

15የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤

ጆሮአቸውም አይሰማም፤

እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣

በጆሮአችው ሰምተው፣

በልባቸውም አስተውለው፣

ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’

16የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን የተባረኩ ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።

18“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ 19የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። 20በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። 21ነገር ግን ሥር መስደድ ባለመቻሉ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። 22በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራውን ሰው ይመስላል። 23በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

የእንክርዳዱ ምሳሌ

24ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። 25ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም አብሮ ብቅ አለ።

27“የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት።

28“እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው።

“አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።

29“እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ 30ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”

Previous
Previous

July 23 2023

Next
Next

July 9 2023