September 3 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 7:5-14
5ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዓሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዛል። 6ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዓሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው። 7ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም። 8በአንድ በኩል ዓሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል። 9እንዲያውም ዓሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዓሥራት ከፍሎአል ማለት ይቻላል፤ 10ምክንያቱም መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር።
ኢየሱስ እንደ መልከጼዴቅ
11ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? 12የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። 13ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። 14ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 2:14-26
እምነትና ሥራ
14ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? 15አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ 16ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል? 17እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።
18ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ይላል።
እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። 19አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ።
20አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? 21አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? 22በዚህም እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ። 23“አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። 24እንግዲህ በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።
25እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 26ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው።
ወንጌል
ሉቃስ 12:16-26
16ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ 17ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።
18“እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’
20“እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው።
21“ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”
አትጨነቁ
22ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ 23ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 25ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው? 26እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ?