September 27 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
1ኛ ጢሞ 5፡ 9~15
ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን
ያስፈልጋል፤ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም
በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።
ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤
የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤ ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት
ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ
አይደሉም። እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም
የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤ ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን
እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕ 3፡ 11~18
ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ
ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ
ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት
በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።
ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና
አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት
ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።
የወንጌል ምንባብ
ማቴ 8፡ 16~27
በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን
ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ
ፈወሰ። ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ። አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር
ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች
መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው።
ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው። ኢየሱስም። ተከተለኝ፥
ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው። ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ
መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥
ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።
ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።