September 20 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
2ኛ ቆሮ 9፡ 1~15
ቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም።
አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን
አነሣሥቶአል። ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው
ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥
ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን
እንድናፍር አይሁን። እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው
ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን
እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ። ይህንም እላለሁ። በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥
በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ
በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል
ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ
ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም
የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ በእኛ በኩል
ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ
በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ
ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ ራሳቸውም ስለ
እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕ 5፡ 1~9
አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም
በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል።
ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥
የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን
እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። እንግዲህ፥
ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን
እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት
ቀርቦአልና። ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት
ቆሞአል።
የወንጌል ምንባብ
ማር 4፡ 24~38
አላቸውም። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም
ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እርሱም አለ።
በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥
እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ
ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ
ይልካል። እርሱም አለ። የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ
እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ
ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ
ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች። መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል
በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ
ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ። ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው። ሕዝቡንም
ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና
ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ
ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።