October 4 2020

የመጀመሪያ ምንባብ

1ኛ ቆሮ 2፡ 1~11

እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን

ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ

ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤

እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን

በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥

ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን

እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን

ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ

ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ

ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም

የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል

ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም

ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ጴጥ 2፡ 20~25

ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን

ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤

ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም

ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል

አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ

ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤*ፍ1* በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች

ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። ፍ1 በግዕዝ እንዲህ ተጽፎአል።

ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፅ በሥጋሁ ከመ ያውፅአነ እምኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ።

የወንጌል ምንባብ

ሉቃ 9፡ 18~27

ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ

ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም። ኤልያስ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት

አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ።

ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ። እርሱ ግን። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት

አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ

አስጠንቅቆ አዘዘ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም

ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ

ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?

በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ

ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ

ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።

Previous
Previous

October 11 2020

Next
Next

September 27 2020