November 15 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 5፡ 10~21
ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ
እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ
በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ሕግ እስከ መጣ ድረስ
ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም፤ ነገር ግን በአዳም መተላለፍ
ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ
ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው
በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው
ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው
ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ
መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት
የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት
ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን
ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ
ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት
በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ
ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።
ሁለተኛ ምንባብ
1ኛ ዮሐ 2፡ 1~17
ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ
ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥
ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ
እንዳወቅነው እናውቃለን። አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ
ውስጥ የለም። ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ
እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ
ይገባዋል። ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ
አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት። ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም
ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን
ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥
የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና። ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ
ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ
ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። ዓለምን
ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ
ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ
ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
የወንጌል ምንባብ
ማቴ 6፡ 5~15
ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን
ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ
መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።
አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።
ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና። እንግዲህ እናንተስ እንዲህ
ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ
ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል
በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም
ለዘለዓለሙ፤ አሜን። ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር
ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።