November 22 2020

የመጀመሪያ ምንባብ

ቆላ 1፡ 12~29

ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥

በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ

እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም

የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ

ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥

በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ

ተፈጥሮአል። እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ

ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። እግዚአብሔር

ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት

ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ

ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን

አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ

ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ

በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ

ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን

እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ

እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ

የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው

የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው

ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን

ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። ለዚህም ነገር ደግሞ፥

በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ጴጥ 1፡ 13~20

ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ

ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት

አትከተሉ። ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ

ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን

አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ

ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር

የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን

እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው

በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።

የወንጌል ምንባብ

ዮሐ 5፡ 16~27

ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ

ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ

አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ

አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት

እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን

ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤

እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም

እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን

እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ

አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን

የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ

አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት

ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ

ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን

ሰጠው።

Previous
Previous

November 29 2020

Next
Next

November 15 2020