November 8 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
ቆላ 1፡ 1~11
በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ጢሞቴዎስም ወንድሙ፥ በቈላስይስ
ለሚኖሩ ቅዱሳንና በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ
ጸጋና ሰላም ይሁን። ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ በሰማይ ከተዘጋጀላችሁ ተስፋ የተነሣ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ
እምነታችሁ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን
ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ስለዚህም ተስፋ በወንጌል እውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም በዓለም
ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ እግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት
ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል። ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ
ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም
በመንፈስ ስለሚሆን ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ
እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም።
በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕ 1፡ 1~12
የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ
ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና
ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን
ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ
የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት
ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው
በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። የተዋረደው
ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር
ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ
ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ
እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
የወንጌል ምንባብ
ማቴ 6፡ 25~34
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት
አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም
አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ
አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ
ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም
አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።
እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥
እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?
ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ
የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም
ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።