March 21 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ቈላስይስ 2፡ 16-23
እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤

እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ዐጒል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድ

ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ

አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ 19ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ

እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋር ግንኙነት የለውም። ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋር

ከሞታችሁ ታዲያ ለምን እንደዚህ ዓለም ሰው ለሕጎቹ ተገዥ ትሆናላችሁ? 21“አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት

ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች

በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጒል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንፃር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው

ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 2፡14-26
ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው

ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ ከእናንተ መካከል

አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን

ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ

አለኝ” ይላል። እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ

ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ

ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ

በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? በዚህም እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ።

“አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር

ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን

ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 26ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ከሥራም የተለየ

እምነት የሞተ ነው።

የወንጌል ምንባብ

ዮሐንስ 2፡13-25
የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን

የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ

ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ

አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል”

ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው። አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት

ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።

አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ

ታነሣዋለህ?” አሉት። ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር። ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን

እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ። በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች

ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤ ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ በሰው ውስጥ

ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

Previous
Previous

March 28 2021

Next
Next

March 14 2021