March 28 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
ገላትያ 5፡1-10
ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። የምለውን
አስተውሉ፤ ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንት እንደማ ይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ። መገረዝ
ለሚፈልግ ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት እንደ ገና ለእያንዳንዱ በግልጽ እናገራለሁ። በሕግ ለመጽደቅ
የምትጥሩ፣ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋ ርቃችኋል። እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን ጽድቅ፣ በመንፈስ አማካይነት
በእምነት ሆነን በናፍቆት እንጠባበቃለን። በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑ፣ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፤
የሚጠቅመውስ በፍቅር የሚገለጽ እምነት ብቻ ነው። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ
እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ
ያቦካል።” የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 5፡13-20
ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል
የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት
የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል። ስለዚህ
ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ
ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል
ዝናብ አልዘነበም። እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ
ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣ ይህን አስተውሉ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት
ያድነዋል፤ ብዙ ኀጢአትንም ይሸፍናል።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐንስ 5፡1-18
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ
መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም
መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ
እየተጠባበቁ፣ ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት
ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን
ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው። ሕመምተኛውም
መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው
ይቀድመኛል” አለው። ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። 9ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም
ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። 10አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለ ሆነ መተኛህን
እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል
መለሰላቸው። እነርሱም፣ “‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ
መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣
“እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። ሰውየውም የፈወሰው
ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው። ወልድ ሕይወትን ይሰጣል አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች
በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው።
እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል
በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።