March 14 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
1ኛ ተሰሎንቄ 4፡1-12
በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ አስተምረናችኋል፤ በርግጥም
እንደዚያው እየኖራችሁ ነው። ስለ ሆነም በጌታ በኢየሱስ የምንለምናችሁና የምንመክራችሁ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በዚሁ
እንድትገፉበት ነው። በጌታ በኢየሱስ ሥልጣን ምን ዐይነት ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ
ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ
ነው፤ ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን። በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን
አያታል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ
የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኵሰት አልጠራንምና። እንግዲህ ይህን ምክር ንቆ
የማይቀበል፣ የናቀው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም። ስለ ወንድማማች መዋደድ
ማንም እንዲጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር
ተምራችኋልና። በመላዪቱ መቄዶንያ የሚገኙትን ወንድሞች ሁሉ እንደምትወዷቸው የታወቀ ነው፤ ነገር ግን ወንድሞች
ሆይ፤ ከዚህ በበለጠ እንድትገፉበት እንመክራችኋለን። ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በገዛ እጃችሁ ሥሩ፤ በጸጥታ ኑሩ፤
በራሳችሁ ጒዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ። 12ይውም በዕለት ተለት ኑሮአችሁ በውጭ ባሉት ዘንድ እንዲያስከብራችሁና በማንም
ሰው ላይ ሸክም እንዳትሆኑ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
1ኛ ጴጥሮስ 1፡13-25
ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ
በሙሉ አድርጉ። ታዛዦች ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር
ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም
ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል። ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ የሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት
ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት
የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን
እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን ግን
በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ። በእርሱም አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር
ታምናላችሁ፤ ስለዚህ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው። እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን
ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት
ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር፣ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። ምክንያቱም
መጽሐፍ እንደሚል፣ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም
ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።
የወንጌል ምንባብ
ማቴዎስ 6፡16-23
“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት
ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን
ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤
በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው
በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ
ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና። “ዐይን
የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ
ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት
ድቅድቅ ይሆን?