January 31 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:13-24

ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን

እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ

አደርጋለሁ። በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥ በእናንተም መካከል ወደ

መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ። እንግዲህ ይህን

ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው

በዓለማዊ ልማድ ነውን? እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም

አይሆንም። በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ

አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል። እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት

በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው። በክርስቶስም ከእናንተ ጋር

የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። እኔ ግን

ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ። ለደስታችሁ

ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ዮሐ 2፡22-29
ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ

ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት

በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። እርሱም

የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት

ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥

እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥

በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ

ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።

የወንጌል ምንባብ

የሉቃስ ወንጌል 2:42-52
የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ

ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው

የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም

ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም

ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥

አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። እርሱም። ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ

አላወቃችሁምን? አላቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥

ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም

በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

Previous
Previous

February 7 2021

Next
Next

January 24 2021