January 24 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ወደ ዕብራውያን 2: 1-10
ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ
ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥
እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ
ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት። ስለ እርሱ
የምንናገርበትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና። ነገር ግን አንዱ በአንድ ስፍራ፡ ታስበው ዘንድ ሰው
ምንድር ነው? ወይስ ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና
ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች
ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ
ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና
የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን። ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ
የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።



ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ዮሐንስ 5: 1-12
ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን
ደግሞ ይወዳል።እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን፡
ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም፡ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ
ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር
ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው
ብቻ አይደለም፡ መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት
ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤
በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። እግዚአብሔርም
የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤
የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።


የወንጌል ምንባብ

ዮሐንስ 2: 1-13
በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ
ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው፡ ኢየሱስም፡ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ
ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው አይሁድም
እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት
እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፡ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ
አፋቸውም ሞሉአቸው፡ አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ
በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ።
ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ
አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም
በእርሱ አመኑ። ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን
ኖሩ፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

Previous
Previous

January 31 2021

Next
Next

January 19 2021