February 7 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ወደ ገላትያ ሰዎች 4:21-31
እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ

ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን

በተስፋው ቃል ተወልዶአል። ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው

አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤

አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር

ናት እርስዋም እናታችን ናት። አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል

ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች

ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን

መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፥

ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡1-8
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን

ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።

በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ

እየቀረባችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ

መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። በመጽሐፍ። እነሆ፥ የተመረጠና

የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ክብሩ

ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ

የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤ የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።

የወንጌል ምንባብ

የሉቃስ ወንጌል 2:42-52
የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ

ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው

የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም

ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም

ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥

አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። እርሱም። ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ

አላወቃችሁምን? አላቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥

ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም

በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

Previous
Previous

February 14 2021

Next
Next

January 31 2021