February 14 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
ወደ ዕብራውያን 12:12-21
ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ
አድርጉ። ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።
የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥
ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው
እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም
ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ
ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው
ለመኑ፤ እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤ ሙሴም። እጅግ
እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤
ሁለተኛ ምንባብ
2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡19-21
ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥
ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ። ይህን
በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው
ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።
የወንጌል ምንባብ
የዮሐንስ ወንጌል 10:34-42
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር
አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ
የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን
ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ። እንግዲህ
ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ። ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ
እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ። ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ
ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።