February 16 2025

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 9:1-16
የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ

1በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም፤ ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። 2ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ። 3ለወገኖቼ ስል ስለ ወንድሞቼ እኔ ራሴ የተረገምሁና ከክርስቶስም ተለይቼ የተጣልሁ እንድሆን እንኳ እወድድ ነበር፤ 4እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ ናቸው፤ ልጅ መሆን፣ መለኮታዊ ክብር፣ ኪዳን፣ ሕግን መቀበል፣ የቤተ መቅደስ ሥርዐትና ተስፋ የእነርሱ ናቸውና። 5አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው፤ አሜን።

6ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ተሽሯል ማለት አይደለም፤ ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለምና። 7ከአብርሃም ዘርም ስለ ሆኑ፣ ሁሉም ልጆቹ አይደሉም፤ ይልቁንስ፣ “ትውልድህ በይሥሐቅ በኩል ይጠራልሃል” እንደ ተባለው ነው። 8ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው። 9“ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ተብሎ ተስፋው ተሰጥቷልና።

10ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይስሐቅ ነው። 11መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣ 12በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁ ታናሹን ያገለግላል” ተብሎ ተነገራት። 13ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

14እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርግም! 15ለሙሴ፣

“የምምረውን እምረዋለሁ፤

ለምራራለትም እራራለታለሁ” ይላልና።

16እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 2:20-25
20ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።

22“እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤

በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።”

23ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ። 24ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በዕንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቍስል እናንተ ተፈውሳችኋል። 25ቀድሞ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።

ወንጌል

ዮሐንስ 4:1-26
ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ጋር ተነጋገረ

1ፈሪሳውያን ከዮሐንስ ይልቅ ኢየሱስ ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዳፈራና እንዳጠመቀ ሰሙ፤ 2ዳሩ ግን ያጠመቀው ኢየሱስ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ። 3ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቅቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ።

4በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት። 5ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። 6በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጕዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር።

7አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ 8ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር።

9ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው።

10ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት።

11ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? 12ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጕድጓድ ጠጥተዋል።”

13ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ 14እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”

15ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው።

16እርሱም፣ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት።

17ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች።

ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤ “ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤ 18በርግጥ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት ነው።”

19ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ፤ 20አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው።

21ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ። 22እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን። 23በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። 24እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”

25ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።

26ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት።

Previous
Previous

February 23 2025

Next
Next

February 9 2025