February 9 2025

የመጀመሪያ ምንባብ

ገላትያ 4:21-31
አጋርና ሣራ ምሳሌ መሆናቸው

21እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? 22አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፏልና። 23ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት። 25እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና። 26ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት። 27እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤

ደስ ይበልሽ፤

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣

በእልልታ ጩኺ፤

ባል ካላት ይልቅ፣

የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው ልጅ፣ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው። 30ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከልጇ ጋር አስወግዳት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋር አይወርስምና” ይላል። 31ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 2:1-8
1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። 2በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ

4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ 5እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣

በጽዮን አኖራለሁ፤

በእርሱም የሚያምን ከቶ አያፍርም።”

7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣

“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8ደግሞም፣

“ሰዎችን የሚያሰናክል፣

የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”

የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

ወንጌል

ዮሐንስ 4:19-27
19 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። 20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። 21 ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። 22 እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። 23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ 24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። 25 ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። 26 ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። 27 በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም።

Previous
Previous

February 16 2025

Next
Next

February 2 2025