February 2 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
2 ቆሮንቶስ 1:13-24
13ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። 14እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ።
15በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር። 16ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁና ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ ስሄድ በጕዞዬ እንድትረዱኝ ዐቅጄ ነበር። 17ይህን ሳቅድ በሚገባ ሳላስብ ያደረግሁት ይመስላችኋልን? ወይስ በዓለማዊ ልማድ አንዴ፣ “አዎን፣ አዎን” ወዲያው ደግሞ፣ “አይደለም፣ አይደለም” የምል ይመስላችኋልን?
18እግዚአብሔር ታማኝ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ለእናንተ የምንናገረው ቃላችን፣ “አዎን” እና “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ 19ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው። 20በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው። 21እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ 22የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።
23ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ እግዚአብሔር ይመስክርብኝ። 24ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 2:22-29
22ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው።
24ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር፤ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። 25ይህ እርሱ የሰጠን ተስፋ የዘላለም ሕይወት ነው።
26ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። 27እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን እውነት እንጂ ሐሰት ያልሆነው የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር እንደሚያስተምራችሁ፣ ያም እውነት እንጂ ሐሰት እንዳልሆነ፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ።
የእግዚአብሔር ልጆች
28እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።
29እርሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።
ወንጌል
ሉቃስ 2:42-52
42ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። 43በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። 44አብሯቸው ያለ መስሏቸው የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ 45ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
46ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ 47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። 48ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔ እኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
49እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። 50እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።
51ከዚያም አብሯቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። 52ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።