February 23 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 13:7-16
7የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው። 8ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።
9በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ እንጂ የምግብ ሥርዐት በመጠበቅ አይደለም፤ ይህን ሥርዐት የሚጠብቁት እንኳ በዚህ አልተጠቀሙም። 10በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን።
11ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል። 12እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ። 13ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። 14ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን።
15ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመስክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ። 16ደግሞም መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 4:6-17
6ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤
ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል”
ያለው ስለዚህ ነው።
7እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ ዕዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
11ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ስለ ነገ መመካት
13እናንተ፣ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። 14ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። 15ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክሕት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል።
ወንጌል
ዮሐንስ 3:10-24
10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? 11እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። 12ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። 14ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ 15ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።
16“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና። 17እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። 18በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። 19ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ 20ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”
መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መሰከረ
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም።
23በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። 24ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር።
ኪዳነ ምሕረት
የመጀመሪያ ምንባብ
ገላትያ 4:1-11
ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ 2 ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። 3 እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ 4 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5 እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። 6 ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። 7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። 8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ 9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት መለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን? 10 ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። 11 ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።
ሁለተኛ ምንባብ
2ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡4-7
4 ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል። 5 አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም። 6 እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት። 7 ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።
ወንጌል
ሉቃስ 1:39-56
ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች
39ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ 42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። 45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”
የማርያም መዝሙር
46ማርያምም እንዲህ አለች፤
“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤
47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤
48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና።
ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ
ብፅዕት ይሉኛል፤
49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ
ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤
50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ
እስከ ትውልድ ይኖራል።
51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤
በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤
52ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤
ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤
ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤
54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን
እስራኤልን ረድቷል፤
55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣
ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።