December 27 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 13፡ 11~14
ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ
እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን
ጋሻ ጦር እንልበስ።
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥
በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ
አታስቡ።
ሁለተኛ ምንባብ
1ኛ ዮሐ 1፡ 1~10
ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም
እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ
የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት
እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም
ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን። ከእርሱም የሰማናት
ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም
የምትል ይህች ናት። ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም
አናደርግም፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም
የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥
እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ
ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ
የለም።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐ 1፡ 1~18
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ
በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ
አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥
ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ
በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥
እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም
ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም
አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ
ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ
ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ
ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ
በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ
ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን
በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ
ልጁ እርሱ ተረከው።