January 3 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብ 13፡ 16~25
ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ

ያሰኘዋልና። ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ

በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ

በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና። ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ

ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን

ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥

በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም

ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ወንድሞች ሆይ፥

የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ፥ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና። ወንድማችን ጢሞቴዎስ

እንደ ተፈታ እወቁ፥ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ። ለዋኖቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ

ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ጴጥ 2፡ 21~25
የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ

መከራን ተቀብሎአልና።

እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም

ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ

እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤*ፍ1* በመገረፉ ቁስል

ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። ፍ1

በግዕዝ እንዲህ ተጽፎአል። ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፅ በሥጋሁ ከመ ያውፅአነ

እምኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ።

የወንጌል ምንባብ

ዮሐ 10፡ 1~21
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ

ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን

ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ

በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ

አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን

እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።

ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ

የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም

እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ

ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን

ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ

ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም

አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።

ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም

መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ

በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን

አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና

መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።

ሌሎችም። ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ።

Previous
Previous

January 6 2021

Next
Next

December 27 2020