December 20 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብ 1፡ 1~11
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ
ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ
መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ
በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ
ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። ከመላእክትስ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት
እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ።
የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። ስለ መላእክትም። መላእክቱን መናፍስት
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ
ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር
አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል። ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን
መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ
ልብስ ያረጃሉ፥
ሁለተኛ ምንባብ
2ኛ ጴጥ 3፡ 1~9
ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ
የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ
እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ። በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ
ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም። የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች
ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም
በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት
ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት
ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን ወዳጆች
ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር
አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ
ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐ 1፡ 44~51
በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና
ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን
የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው። ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ
ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ።
ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ። ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው።
ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው። ናትናኤልም መልሶ። መምህር
ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው። ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች
አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ
ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለ