December 13 2020
የመጀመሪያ ምንባብ
1ኛ ቆሮ 15፡ 12~32
ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ። ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት
ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ
ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም። ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ
መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን
አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤
እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች
ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ
ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል
ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን
እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት
ናቸው፤ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን
ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ
ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ
ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ
በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን
የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ
ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት
እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ። እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ
የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ።
ሁለተኛ ምንባብ
2ኛ ጴጥ 3፡ 1~10
ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ
የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ
እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ። በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ
ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም። የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች
ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም
በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት
ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት
ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን ወዳጆች
ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር
አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ
ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ
ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥
ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።
የወንጌል ምንባብ
ሉቃ 12፡ 32~40
አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ
ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን
የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው
እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ
የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል
ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥
እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥
ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት
ይመጣልና።