August 28 2022
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 3:1-19
ኢየሱስ ከሙሴ በላይ ነው
1እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። 2ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ ታማኝ እንደ ነበር፣ እርሱም ለሾመው ታማኝ ነበር። 3ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቶአል፤ 4እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። 5ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ 6ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።
ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
7ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
8በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
ልባችሁን አታደንድኑ።
9አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤
መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ።
10በዚያም ትውልድ ላይ የተቈጣሁት ለዚህ ነበር፤
እንዲህም አልሁ፤ ‘ልባቸው ሁል ጊዜ ይስታል፤
መንገዴንም አላወቁም፤’
11ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤
“ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም።”
12ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 13ነገር ግን ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ። 14በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንይዝ ከክርስቶስ ጋር ተካፋዮች እንሆናለን፤ 15ይኸውም፣
“ዛሬ ድምጹን ብትሰሙ፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
አሁንም ልባችሁን አታደንድኑ” እንደ ተባለው ነው።
16ሰምተው ያመፁት እነማን ነበሩ? ሙሴ ከግብፅ መርቶ ያወጣቸው ሁሉ አይደሉምን? 17አርባ ዓመት የተቈጣውስ እነማንን ነበር? ኀጢአት ሠርተው ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረውን አይደለምን? 18ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደሆነ እንረዳለን።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 5:1-11
ለጨካኝ ሀብታሞች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለ ሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። 2ሀብታችሁ ሻግቶአል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። 3ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። 4ልብ በሉ፤ እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የአጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሶአል። 5በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል ኖራችኋል፤ ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። 6እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሐን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም።
በመከራ ውስጥ መታገሥ
7እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። 8እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል። 9ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ ያለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል።
10ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። 11በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።
ወንጌል
ዮሐንስ 6:41-71
41አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጒረመርሙበት ጀመር። 42ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’” አሉ።
43ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ 44የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 45በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። 47እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። 48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። 50ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። 51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
52አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር።
53ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ 55ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ 56ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። 58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” 59ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኲራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።
ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል ተዉ
60ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።
61ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጒረም ረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን? 62ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? 63መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤ 64ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው። 65ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ።
66ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።
67ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
68ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ 69አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።”
70ኢየሱስም መልሶ፣ “ዐሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። 71የአስቆሮቱ የስምዖን ልጅ ይሁዳ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም፣ ኋላ አሳልፎ ስለሚሰጠው ስለ እርሱ መናገሩ ነበር።