August 21 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 12:18-31
18
ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ እያንዳንዱን በየቦታው መድቦአል። 19ሁሉም አንድ ብልት ቢሆን ኖሮ አካል ከየት ይገኝ ነበር? 20እንግዲህ ብልቶች ብዙ ናቸው፣ አካል ግን አንድ ነው።

21ዐይን እጅን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። 22እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ብልቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። 23የተናቁ ለሚመስሉን ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ደግሞም የምናፍርባቸውን ብልቶች ይበልጥ እንንከ ባከባቸዋለን፤ 24የማናፍርባቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጐድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቶአቸዋል፤ 25ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። 26አንድ ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር ሌሎቹም ብልቶች አብረው ደስ ይላቸዋል።

27እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ። 28እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንደኛ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛ ነቢያትን፣ ሦስተኛ መምህራንን፣ ቀጥሎም ታምራት አድራጊዎችን፣ የመፈወስ ስጦታዎች ያላቸውን፣ ሌሎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፣ የማስተዳደር ስጦታ ያላቸውንና በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር ስጦታ ያላቸውን ሰዎች መድቦአል። 29ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ መምህራን ናቸውን? ሁሉስ ታምራት ያደርጋሉን? 30ሁሉስ የመፈወስ ስጦታዎች አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጒማሉን? 31ነገር ግን ከሁሉ የሚበልጠውን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።

ሁለተኛ ምንባብ

ይሁዳ 1:17-25
ጸንቶ ስለ መቆም የቀረበ ጥሪ

17ነገር ግን ወዳጆች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን አስታውሱ። 18እነርሱም፣ “በመጨረሻው ዘመን ርኩስ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ” ብለዋችኋል። 19እነዚህ ሰዎች በመካከላችሁ መለያየትን የሚፈጥሩ፣ በደመ ነፍስ የሚነዱ መንፈስ የሌላቸው ናቸው።

20እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ። 21ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።

22ተጠራጣሪ ለሆኑት ራሩላቸው፤ 23አንዳንዶችን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኗቸው፤ ለሌሎች ደግሞ በርኩስ ሥጋ የተበከለውን ልብሳቸውን እንኳ እየጠላችሁ በፍርሀት ምሕረት አሳዩአቸው።

ቃለ ውዳሴ

24እንዳትወድቁ ሊጠብቃችሁና ያለ ነቀፋና በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው፣ 25እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለምም ድረስ ክብር፣ ግርማ፣ ኀይልና ሥልጣን ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ማቴዎስ 10:1-14
የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ

1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።

2የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣ 3ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣ 4ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ።

5እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ። 6ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። 7ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ። 8በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ። 9በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ። 10ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና።

11“ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ። 12ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ። 13ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ። 14ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።

Previous
Previous

August 28 2022

Next
Next

August 14 2022