September 4 2022
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 13:1-14
ባለ ሥልጣናትን መታዘዝ
1ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። 2ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ። 3ገዦች ክፉ ለሚሠሩ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያስ መልካሙን አድርግ፤ እርሱም ያመሰግንሃል፤ 4እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም፤ ክፉ የሚያደርገውን ለመቅጣት የቊጣ መሣሪያ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። 5ስለዚህም ቅጣትን በመፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ለኅሊና ሲባል ለባለ ሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው።
6ግብር የምትከፍሉትም ደግሞ ለዚህ ነው፤ ባለ ሥልጣናቱ፣ በዚሁ ተግባር ላይ የተሠማሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና፤ 7ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ።
ጊዜው ተቃርቦአልና ተዋደዱ
8እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድ እርሱ ሕግን ፈጽሞአልና። 9“አታመንዝር”፣ “አትግደል”፣ “አትስረቅ”፣ “አትመኝ” የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዛት ቢኖሩም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃለዋል። 10ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው። 11ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቦአልና። 12ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ። 13በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። 14ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 2:2-10
2በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።
ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ
4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ 5እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤
“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣
በጽዮን አኖራለሁ፤
በእርሱም የሚያምን፣ ከቶ አያፍርም።”
7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣
“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣
እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”
8ደግሞም፣ “ሰዎችን የሚያሰናክል፣
የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”
የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።
9እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ። 10ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
ወንጌል
ማቴዎስ 4:12-16
ኢየሱስ ስብከት መጀመሩ
12ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ተመለሰ። 13የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፣ በዛብሎንና በንፍታሌም አካባቢ በባሕሩ አጠገብ በምትገኘው በቅፍርናሆም ከተማ መኖር ጀመረ። 14በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፤
15“የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣
ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣
ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣
16በጨለማ የሚኖር ሕዝብ፣
ታላቅ ብርሃን አየ፤
በሞት ጥላ ምድር ላለው፣
ብርሃን ወጣለት።”