September 14 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 11:17-34
የጌታ እራት
17ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚጐዳ እንጂ ለሚጠቅም ስላልሆነ፣ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ እያመሰገንኋችሁ አይደለም። 18ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ። 19ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው። 20በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤ 21በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል። 22ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።
23እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ ዐልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ 24ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 26ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።
27እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል። 28ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤ 29ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣልም። 30ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው። 31ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር። 32ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኰነን ነው።
33ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ፣ ማንም የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ።
ስለ ቀረው ነገር ደግሞ በምመጣበት ጊዜ እደነግጋለሁ።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 2:1-13
አድልዎ ማድረግ አይገባም
1ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደ መሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። 2የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ 3ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም ስፍራ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ 4በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን?
5የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? 6እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? 7በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን?
8በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው። 9አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤ 10ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቈጠራል። 11“አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደልም” ብሏልና። ባታመነዝር፣ ነገር ግን ብትገድል፣ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል።
12ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፤ 13ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል።
ወንጌል
ዮሐንስ 1:15-37
15ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። 16ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ 17ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። 18ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።
መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ
19አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር።
20ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ።
21እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት።
እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ።
እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት።
እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ።
22በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት።
23ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።
24ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ 25“ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት።
26ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።”
28ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።
የእግዚአብሔር በግ
29ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ 30‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ 31እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።”
32ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ 33በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ 34አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።”
የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት
35በማግስቱም፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ 36ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር በግ!” አለ።
37ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።
September 7 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 1:1-9
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስ፣ ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፤
2በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ተቀድሰው፣ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤
3ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ምስጋና
4በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 5ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በእርሱ በልጽጋችኋል፤ 6ስለ ክርስቶስ የመሰከር ንላችሁም በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። 7ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጒጒት በመጠባበቅ ላይ ሳላችሁ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም። 8በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትገኙ እርሱ እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንቶ ይጠብቃችኋል። 9ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
2 ጴጥሮስ 3:10-18
10የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል።
11እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ 12ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። 13እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።
14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። 15የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ 16እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
17እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። 18ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ሉቃስ 17:11-37
ከለምጽ የነጹ ዐሥር ሰዎች
11ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኵል ዐለፈ፤ 12ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ 13በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት።
14እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ።
15ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ 16በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።
17ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? 18ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?”። 19ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት
20ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ 21ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።”
22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። 23ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ 24ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። 25ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል።
26“በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። 27ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።
28“በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ 29ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።
30“የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። 31በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። 32የሎጥን ሚስት አስታውሱ። 33ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል። 34እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። 35ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። 36ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ አብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”
37እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት።
እርሱም፣ “ጥንብ ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።
August 31 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 3:1-19
ኢየሱስ ከሙሴ በላይ ነው
1እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። 2ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ ታማኝ እንደ ነበር፣ እርሱም ለሾመው ታማኝ ነበር። 3ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቷል፤ 4እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። 5ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ 6ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።
ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
7ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
8በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
ልባችሁን አታደንድኑ።
9አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤
መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ።
10በዚያም ትውልድ ላይ የተቈጣሁት ለዚህ ነበር፤
እንዲህም አልሁ፤ ‘ልባቸው ሁልጊዜ ይስታል፤
መንገዴንም አላወቁም፤’
11ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤
‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም።’ ”
12ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 13ነገር ግን ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታልሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ። 14በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንይዝ ከክርስቶስ ጋር ተካፋዮች እንሆናለን፤ 15ይኸውም፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
አሁንም ልባችሁን አታደንድኑ”
እንደ ተባለው ነው።
16ሰምተው ያመፁት እነማን ነበሩ? ሙሴ ከግብፅ መርቶ ያወጣቸው ሁሉ አይደሉምን? 17አርባ ዓመት የተቈጣውስ እነማንን ነበር? ኀጢአት ሠርተው ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረውን አይደለምን? 18ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደ ሆነ እንረዳለን።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 5:1-11
ለጨካኝ ሀብታሞች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። 2ሀብታችሁ ሻግቷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። 3ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። 4ልብ በሉ፤ ዕርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የዐጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሷል። 5በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል ኖራችኋል፤ ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። 6እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሓን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም።
በመከራ ውስጥ መታገሥ
7እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። 8እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል። 9ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ፤ ፈራጁ በበር ላይ ቆሟል።
10ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። 11በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።
ወንጌል
ዮሐንስ 6:41-71
41አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጕረመርሙበት ጀመር። 42ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’ ” አሉ።
43ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ 44የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 45በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። 47እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። 48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። 50ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። 51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
52አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር።
53ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ 55ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ 56ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። 58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” 59ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኵራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።
ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል ተዉ
60ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።
61ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጕረምረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን? 62ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? 63መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤ 64ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው። 65ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ።
66ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።
67ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
68ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ 69አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።”
70ኢየሱስም መልሶ፣ “ዐሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። 71የአስቆሮቱ የስምዖን ልጅ ይሁዳ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም፣ ኋላ አሳልፎ ስለሚሰጠው ስለ እርሱ መናገሩ ነበር።
August 24 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ፊልጵስዩስ 3:1-5
በሥጋ አለመመካት
1ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ፣ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል። 2ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ። 3እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና። 4ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ።
ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤ 5በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ዘር፣ ከብንያም ወገን የተወለድሁ ስሆን፣ ከዕብራውያንም ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ከተነሣ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 2:1-20
1ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።
3ትእዛዞቹን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። 4“እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ 6ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።
7ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው።
9በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። 10ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። 11ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።
12ልጆች ሆይ፤
ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣
እጽፍላችኋለሁ።
13አባቶች ሆይ፤
ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
14አባቶች ሆይ፤
ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣
እጽፍላችኋለሁ።
ጐበዛዝት ሆይ፤
ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣
የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣
ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣
እጽፍላችኋለሁ።
ዓለምን አትውደዱ
15ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
ከክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጠንቀቅ
18ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደ ሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።
19ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።
20እናንተ ግን ከእርሱ፣ ከቅዱሱ ቅባት አላችሁና፣ ሁላችሁም እውነትን ታውቃላችሁ።
ወንጌል
ማቴዎስ 15:6-20
6‘አንድ ሰው ይህን ካደረገ ዘንድ አባቱን ወይም እናቱን አክብሯል’ ትላላችሁ። ስለዚህ ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ። 7እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤
8“ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
9በከንቱ ያመልኩኛል፣
ትምህርታቸውም የሰው ሥርዐት ነው።’ ”
10ሕዝቡን ወደ እርሱ ቀረብ እንዲሉ አድርጎ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ፤ አስተውሉም፤ 11ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም።”
12ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ያልኸውን ሰምተው እንደ ተቈጡ ዐወቅህ?” አሉት።
13እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14ተዉአቸው፣ እነርሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውር መሪዎች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ተያይዘው ገደል ይገባሉ።”
15ጴጥሮስም፣ “ምሳሌውን አስረዳን” አለው።
16እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተም እስካሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን? 17በአፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ዘልቆ፣ ከዚያም ወደ ውጭ እንደሚወጣ አታውቁምን? 18ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይመነጫል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው፤ 19ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫሉና። 20ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን አያረክስም።”
August 17 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 6:12-23
12ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።
የጽድቅ ባሮች
15እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን? በጭራሽ አይገባም! 16ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምት ታዘዙት ለእርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደሆናችሁ አታውቁምን? 17ነገር ግን የኀጢአት ባሮች የነበራችሁ ቢሆንም፣ ለተሰጣችሁለት ትምህርት በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ 18ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ፣ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።
19በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኵሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ። 20የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ። 21አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው። 22አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። 23የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 4:1-17
ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ
1በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ምኞታችሁ አይደለምን? 2ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም። 3ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና።
4አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? 6ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤
ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል”
ያለው ስለዚህ ነው።
7እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
11ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ስለ ነገ መመካት
13እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። 14ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። 15ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል።
ወንጌል
ዮሐንስ 7:32-52
32ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጒምጒ ምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው።
33ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋር የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ 34ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።”
35አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? 36‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤’ ደግሞም፣ ‘እኔ ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”
37የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ 38በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” 39ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀ በሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።
40ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ።
41ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ።
ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? 42መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” 43ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ 44አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም።
የአይሁድ መሪዎች አለማመን
45በመጨረሻም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ፣ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም ጠባቂዎቹን፣ “ለምን አላመጣችሁትም?” አሏቸው።
46ጠባቂዎቹም፣ “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ።
47ፈሪሳውያንም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተም ተታላችኋል ማለት ነው? 48ለመሆኑ ከባለሥልጣኖችና ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለ? 49ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።”
50ከዚህ ቀደም ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከእነርሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፤ 51“ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?”
52እነርሱም፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምር፤ ትደርስበታለህ” ብለው መለሱለት።
August 10 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 8:1-13
ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ
1ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም። 3እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።
4እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፤ 6ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
7ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። 8ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።
9ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ። 10አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን? 11ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው። 12በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 4:1-5
ለእግዚአብሔር መኖር
1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።
ወንጌል
ማቴዎስ 12:38-50
ማረጋገጫ ምልክት ስለ መሻት
38ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት።
39እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። 40ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። 41የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። 42በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።
43“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። 44ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። 45ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”
የኢየሱስ እናትና ወንድሞች
46ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። 47አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።
48ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። 49በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ 50በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”
August 3 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ቲቶ 3:1-15
በጎ የሆነውን ማድረግ
1ሰዎች ለገዦችና ለባለ ሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው። 2እንዲሁም በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ አስገንዝባቸው።
3ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኝነት እንኖር ነበር። 4ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ 5ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ 6ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ 7ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው። 8ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።
9ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና። 10መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ። 11እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ።
የመጨረሻ ምክር
12አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ እንደ ላክሁ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጵልዮን ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ላሳልፍ ወስኛለሁ። 13ሕግ ዐዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን በጒዟቸው ለመርዳት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ አሟላላቸው። 14ከእኛ ወገን ለሆኑት ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙና ኑሮአቸውም ፍሬ የሌለው እንዳይሆን ለመልካም ሥራ መትጋትን ይማሩ ዘንድ ይገባቸዋል።
15ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ከእምነት የተነሣ ለሚወዱን ሰላምታ አቅርቡልን።
ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 4:6-11
6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።
7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ማርቆስ 6:47-56
47በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። 48ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። 49ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሎአቸው ጮኹ፤ 50ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። 51እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሮአቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤ 52የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር።
53በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ። 54ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ 55ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። 56በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።
July 27 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
2 ቆሮንቶስ 9:1-15
1ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቶአል። 3እንግዲህ በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ወንድሞችን ልኬአለሁ። 4ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ያን ያህል በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን። 5ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።
በልግስና መስጠት
6ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል። 7እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል። 8ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ 9ይህም፣
“በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል”
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
10ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። 11ሁል ጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።
12ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጒድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው። 13የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ስለ ታዘዛችሁና ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ስላሳያችሁት ልግስና ሰዎች ተፈትኖ ስላለፈው አገልግሎታችሁ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ 14ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ይናፍቋችኋል። 15በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:15-22
15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ማቴዎስ 24:36-51
የሚመጣበት ቀንና ሰዓት አለመታወቁ
36“ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። 37ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ 38ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ 39እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። 40በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። 41ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።
42“እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። 43ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። 44የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።
45“በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ እንግዲህ ማነው? 46ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤ 47እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48ነገር ግን ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ 49ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ 51ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
July 20 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
2 ቆሮንቶስ 10:1-18
ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ
1እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ። 2ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በዓለማዊ መንገድ እንደምንኖር አድርገው በሚቈጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር ቈርጫለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ዐይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3የምንኖረው በዚህ ዓለም ቢሆንም፣ የምንዋጋው በዚህ ዓለም ስልት አይደለም። 4ደግሞም የምንዋጋበት የጦር መሣሪያ የዚህ ዓለም መሣሪያ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደምሰስ የሚችል መለኮታዊ ኀይል ያለው ነው። 5በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን። 6መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ አለ መታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት ተዘጋጅተናል።
7እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል። 8ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበል ነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና። 9በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። 10አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ። 11እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።
12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመ ዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያነጻ ጽሩ አስተዋዮች አይደሉም። 13እኛ ግን ከመጠን በላይ አንመካም፤ የምንመካው እግዚአብሔር በመደበልንና እስከ እናንተም እንኳ በሚደርሰው የአገልግሎታችን ወሰን ነው። 14የክርስቶስን ወንጌል ይዘን ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ፣ ከተመደበልን የአገልግሎት ወሰን አላለፍንም። 15ደግሞም ሌሎች በደከሙበት ሥራ ከመጠን በላይ በመመካት ከተመደበልን ወሰን አናልፍም፤ ይልቁንም እምነታችሁ እያደገ በሄደ ቍጥር በእናንተ ዘንድ የተመደበልን አገልግሎት እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን። 16ስለዚህ በሌላው ሰው ክልል አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ሳንመካ፣ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር ወንጌልን መስበክ እንችላለን። 17ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤ 18ምክንያቱም ጌታ ራሱ የሚያመሰግነው እንጂ፣ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ተቀባይነት አይኖረውም።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 3:1-8
አንደበትን መግታት
1ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። 2ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
3ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። 4ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። 5እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ 6ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች።
7ማናቸውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። 8ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት።
ወንጌል
ማቴዎስ 8:1-34
የለምጻሙ መንጻት
1ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።
3ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 4ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው።
የመቶ አለቃው እምነት
5ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ 6“ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቶአል” አለው።
7ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።
8የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ 9እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።”
10ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ 11እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ 12መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
13ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።
ኢየሱስ ብዙዎችን መፈወሱ
14ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጎራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታማ ተኝታ አገኛት። 15እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው።
16በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። 17በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤
“እርሱ ደዌያችንን ተቀበለ፤
ሕመማችንንም ተሸከመ።”
የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ውሳኔ ይጠይቃል
18ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። 19በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
20ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።
21ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።
22ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
23ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። 24ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። 25ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።
26ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ።
27ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።
ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች
28ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። 29እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።
30ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 31አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። 32ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። 33የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። 34እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት።
July 13 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 6:7-20
7ዘወትር በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። 8ነገር ግን እሾህና አሜኬላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቦአል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው።
9ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋር የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። 10እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። 11የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 12በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።
የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ርግጠኛነት
13እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ 14እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” 15አብርሃምም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ የተሰጠውን ተስፋ አገኘ።
16ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላውም የተባለውን ነገር ስለሚያጸና፣ በመካከላቸው የተነሣው ክርክር ሁሉ ይወገዳል። 17እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው፤ 18እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጎአል። 19እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። 20ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:8-14
መልካም በማድረግ መከራን መቀበል
8በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ። 9ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። 10ስለዚህ፣
“ሕይወትን የሚወድ፣
መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣
ምላሱን ከክፉ፣
ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።
11ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤
ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤
12ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤
ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤
የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”
13መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? 14ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።
ወንጌል
ማቴዎስ 13:1-30
የዘሪው ምሳሌ
1በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር አጠገብ ተቀመጠ። 2ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቶአቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። 3ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። 6ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። 7አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን አንቆ አስቀረው፤ 8ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”።
10ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት።
11እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤
“እያዩ ስለማያዩ፣
እየሰሙ ስለማይሰሙ ወይም ስለማያስተውሉ ነው።
14እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤
“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤
ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።
15የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤
ጆሮአቸውም አይሰማም፤
እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤
ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣
በጆሮአችው ሰምተው፣
በልባቸውም አስተውለው፣
ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’
16የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን የተባረኩ ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።
18“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ 19የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። 20በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። 21ነገር ግን ሥር መስደድ ባለመቻሉ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። 22በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራውን ሰው ይመስላል። 23በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”
የእንክርዳዱ ምሳሌ
24ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። 25ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም አብሮ ብቅ አለ።
27“የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት።
28“እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው።
“አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።
29“እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ 30ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”
July 6 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 15:33-50
33አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” 34ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።
የትንሣኤ አካል
35ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። 36አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። 37የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። 38እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። 40እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው። 41የፀሓይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል።
42የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ 43በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል፤ 44ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል።
ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። 45ስለዚህ፣ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፏል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። 46ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። 47የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። 48ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። 49የምድራዊውን ሰው መልክ እንደ ለበስን፣ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን።
50ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 5:16-20
16ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል።
17ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። 18እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች።
19ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣ 20ይህን አስተውሉ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድነዋል፤ ብዙ ኀጢአትንም ይሸፍናል።
ወንጌል
ሉቃስ 8:1-21
የዘሪው ምሳሌ
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ ዐለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ 2እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ 3የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።
4ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ 5“አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። 6አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። 7ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። 8ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።”
ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
9ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። 10እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣
“ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣
እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’
11“እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። 12በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። 13በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። 14በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። 15በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት
16“መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 17የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና። 18እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
የኢየሱስ እናትና ወንድሞች
19ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም። 20በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።
21እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።
June 29 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 5:12-21
ሞት በአዳም፣ ሕይወት በክርስቶስ
12ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። 14ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።
15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! 16ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!
18ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።
20ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ 21ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
3 ዮሐንስ 1:1-15
1ሽማግሌው፤
በእውነት ለምወድደው ለውድ ወዳጄ ለጋይዮስ፤
2ወዳጅ ሆይ፤ ነፍስህ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለች ሁሉ መልካም ጤንነት እንዲኖርህና በነገር ሁሉ እንዲሳካልህ እጸልያለሁ። 3ለእውነት ታማኝ እንደ ሆንህና የምትመላለሰውም በእውነት እንደ ሆነ አንዳንድ ወንድሞች መጥተው ስለ አንተ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። 4ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም።
5ወዳጅ ሆይ፤ ለአንተ እንግዶች ቢሆኑም እንኳ፣ ለወንድሞች በምታደርገው ነገር ሁሉ ታማኝ ነህ። 6እነርሱ አንተ ስላለህ ፍቅር በቤተ ክርስቲያን ፊት መስክረዋል፤ በመንገዳቸውም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ 7ስለ ስሙ የወጡት ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ነውና። 8እንግዲህ አብረን ለእውነት እንድንሠራ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ልናስተናግድ ይገባናል።
9ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ መሆን የሚወድደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። 10ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ፤ ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሏቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፤ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል።
11ወዳጅ ሆይ፤ መልካም የሆነውን እንጂ ክፉውን አትምሰል። መልካም የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። ክፉ የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። 12ለድሜጥሮስ፣ ሰው ሁሉ ይመሰክርለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛ ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ እናንተም ምስክርነታችን እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
13የምጽፍልህ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በቀለምና በብርዕ እንዲሆን አልፈልግም። 14በቅርቡ ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊትም እንነጋገራለን።
15ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለወዳጆች በየስማቸው ሰላምታ አቅርብልኝ።
ወንጌል
ማቴዎስ 22:1-22
በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ
1ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ 2“መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ 3ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ።
4“እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ።
5“ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። 7ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።
8“ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ 9ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ 10አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።
11“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ 12እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም።
13“ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ 14የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
ግብር ስለ መክፈል
15ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። 16ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ 17ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”
18ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? 19ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። 20እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።
21እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት።
እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
22ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።
June 22 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 14:1-25
የትንቢትና የልሳን ስጦታዎች
1ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። 2በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለ ሚናገር የሚረዳው የለም። 3ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። 4በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። 5ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፣ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።
6እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ? 7እንደ ዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? 8ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ ትርጒም ያለው ቃል ካልወጣ፣ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። 10በዓለም ላይ ብዙ ዐይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለውም ቋንቋ የለም። 11እንግዲህ አንድ ሰው የሚናገረውን ቋንቋ ትርጒሙን ካላወቅሁ፣ ለሚናገረው እንግዳ እሆንበታለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆንብኛል። 12እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት የምትሹ በመሆናችሁ፣ ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ።
13ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። 14በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 15ታዲያ፣ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። 16እንዲህማ ካልሆነ እግዚአብሔርን በመንፈስ በምታመሰግንበት ጊዜ፣ ለነገሩ እንግዳ የሆነ ሰው አንተ የምትናገረውን ካልተረዳ፣ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፣ “አሜን” ሊል ይችላል? 17አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም።
18ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 19ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።
20ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ፤ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ። 21በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤
“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፣
በባዕዳንም አንደበት፣
ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤
ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፤”
ይላል ጌታ።
22ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 23እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፣ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፣ አብደዋል አይሉምን? 24ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሣል፤ በሁሉ ይመረመራል፤ 25በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፣ “እግዚአብሔር በርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 4:1-8
መናፍስትን መርምሩ
1ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 2የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚቀበል መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ 3ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።
4ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል። 5እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ የሚናገሩት እንደ ዓለም ነው፤ ዓለምም ይሰማቸዋል። 6እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።
የእግዚአብሔር ፍቅርና የሰው ፍቅር
7ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። 8የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።
ወንጌል
ዮሐንስ 15:17-27
17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት።
ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ
18“ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። 19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። 20‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። 21የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። 22መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። 24ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል። 25ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።
26“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ
June 15 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ኤፌሶን 4:1-16
በክርስቶስ አካል ያለ አንድነት
1እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። 2ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። 3በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ 6ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።
7ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። 8ስለዚህም እንዲህ ይላል፤
“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣
ምርኮ ማረከ፤
ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።”
9ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? 10ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። 11አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ 12ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ 13ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው።
14ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። 15ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤ 16ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 2:1-17
1ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።
3ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። 4“እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ 6ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።
7ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው። 9በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። 10ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። 11ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።
12ልጆች ሆይ፤
ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣
እጽፍላችኋለሁ።
13አባቶች ሆይ፤
ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
14አባቶች ሆይ፤
ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣
እጽፍላችኋለሁ።
ጐበዛዝት ሆይ፤
ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣
የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣
ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣
ጽፍላችኋለሁ።
ዓለምን አትውደዱ
15ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
ወንጌል
ዮሐንስ 14:1-21
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታ
1“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። 3ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። 4እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”
ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ
5ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።
6ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”
8ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።
9ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። 12እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። 13አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ 14ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።
ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ተስፋ
15“ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። 16እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሮአችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። 18ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። 21የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
June 8 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 15:20-40
20ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። 21ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። 22ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ 23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። 24ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ 27“ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሎአልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።
29ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? 30እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? 31ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። 32በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤
“ነገ ስለምንሞት፣
እንብላ፣ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው።
33አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” 34ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።
የትንሣኤ አካል
35ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። 36አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። 37የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። 38እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። 40እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 1:1-12
1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኝነት ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ምርጦች፤ 2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤
ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ሕያው ስለ ሆነው ተስፋ ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና
3የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ 4እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን። 5እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። 6አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። 7እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንደተረጋገጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። 8እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል፤ 9የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
10ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ 11በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። 12አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ባበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
ወንጌል
ዮሐንስ 20:1-18
ኢየሱስ ከሞት ተነሣ
1በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። 2ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።
3“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። 5ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። 6ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ 7እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። 8ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ 9ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።
ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ
10ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ 11ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። 12የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች።
13እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።
እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። 14ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም።
15እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት።
እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው።
16ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት።
እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው።
17ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።
18መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።
June 1 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 10:1-21
ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። 2ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም። 3ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። 4ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
5ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። 6ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7“ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። 8ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ 9“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። 10የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። 11መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” 12በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ 13“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
14ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? 15ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
16ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና። 17እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው። 18ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤
“ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣
ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።”
19ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤
“ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናቸዋለሁ፤
ማስተዋል በሌለው ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ”
20ኢሳይያስም በድፍረት፣
“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤
ላልጠየቁኝ ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል።
21ስለ እስራኤል ግን፣
“ወደማይታዘዝና እሺ ወደማይል ሕዝብ፣
ቀኑን ሙሉ እጄን ዘረጋሁ” ይላል።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:15-22
15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ሉቃስ 24:45-53
45በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ 47ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
የኢየሱስ ዕርገት
50ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ 53እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።
May 25 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 4:14-25
14በሕግ የሚኖሩት ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት የማይጠቅም፣ ተስፋም ከንቱ በሆነ ነበር፤ 15ሕግ ቊጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም።
16ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቶአል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የእርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው፤ 17ይህም “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው።
18“ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ። 19እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም። 20ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ 21እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር። 22ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።” 23“ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለእርሱ ብቻ አይደለም፤ 24ነገር ግን እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ ለሚቈጥርልን፣ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው በእርሱ ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው። 25እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።
ሁለተኛ ምንባብ
ራእይ 20:1-15
የሺህ ዓመቱ መንግሥት
1የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው። 3ሺሁ ዓመትም እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።
4ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለእርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግምባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ። 5የቀሩት ሙታን ግን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። 6በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።
የሰይጣን የመጨረሻ ዕጣ
7ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ 8በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፦ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። 9እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው። 10ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።
ሙታን ተፈረደባቸው
11ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። 13ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት። 14ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።
ወንጌል
ዮሐንስ 21:1-14
ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው
1ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ 2ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ 3ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም።
4ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።
5እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው።
እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።
6እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው።
7ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ። 8ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። 9ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ።
10ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው።
11ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። 12ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። 13ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤
ዓሣውንም ሰጣቸው። 14እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።
May 18 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 6:1-14
ለኀጢአት መሞት፣ በክርስቶስ ሕያው መሆን
1እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር? 2ከቶ አይሆንም፤ ለኀጢአት ሞተናል፤ ታዲያ እንዴት አድርገን ከእንግዲህ በእርሱ እንኖራለን? 3ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንድንሆን የተጠመቅን፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? 4ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር ተቀብረናል።
5በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን። 6ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ 7ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቷል።
8ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን። 9ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጕልበት አይኖረውም። 10በሞተ ጊዜ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኀጢአት ሞቷል፤ ነገር ግን በሕይወት መኖርን ለእግዚአብሔር ይኖራል።
11እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቍጠሩ። 12ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 4:4-11
4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።
7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና፣ ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጕረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ዮሐንስ 21:15-25
ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ቀድሞ ቦታው መለሰው
15በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወድደኛለህን?” አለው።
እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።
ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።
16ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወድደኛለህን?” አለው።
እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።
ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።
17ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወድደኛለህን?” አለው።
ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ “ትወድደኛለህን?” ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድድህም ታውቃለህ” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። 18እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” 19ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።
20ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ እራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። 21ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ።
22ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። 23በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሠራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።
24ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
25ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።
May 11 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
ቈላስይስ 3:1-25
የቅድስና ሕይወት መመሪያ
1እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ 2አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። 3ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮአልና፤ 4ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።
5ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። 6በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ 7እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ 8አሁን ግን ቊጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ 9አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። 10የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ 11በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
12እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደመሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ 13እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። 14በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
15እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። 16የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
የክርስቲያናዊ ቤተ ሰብ መመሪያ
18ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ታዘዙ።
19ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው።
20ልጆች ሆይ፤ ይህ ጌታን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ ለወላጆቻችሁ በሁሉም ነገር ታዘዙ፤
21አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።
22ባሮች ሆይ፤ ሰውን ለማስደሰትና ለታይታ ብላችሁ ሳይሆን በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ። 23የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ 24ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው። 25በደለኛውም የእጁን ያገኛል፤ አድልዎም የለም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:15-22
15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ሉቃስ 24:33-44
23ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። 24ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”
25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ 26ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” 27ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
28ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።
30አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። 31በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።
33በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ 34“እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። 35ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ
36ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
37እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? 39እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”
40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። 42እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤ 43እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።
44እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።
May 4 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
2 ቆሮንቶስ 5:11-21
የማስታረቅ አገልግሎት
11እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራለን። የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናችሁ ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። 12ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው። 13ከአእምሮ ውጪ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው። 14የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል። 15በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።
16ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በውጫዊ ነገር አንመዝንም፤ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን በዚህ መልክ መዝነነው ነበር፤ ከእንግዲህ ግን እንደዚህ አናደርግም። 17ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል። 18ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ 19እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን። 20ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። 21እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።
ሁለተኛ ምንባብ
2 ጴጥሮስ 3:14-18
14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። 15የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ 16እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
17እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። 18ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ሉቃስ 24:13-32
በኤማሁስ መንገድ ላይ
13በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። 15እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ 16ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር።
17እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። 18ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት።
19እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ 20እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። 21እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። 22ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ 23ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። 24ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”
25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ 26ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” 27ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
28ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።
30አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። 31በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።