July 26 2026
የመጀመሪያ ምንባብ
1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2 :1-12
የጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ
1ወንድሞች ሆይ! እናንተን መጎብኘታችን በከንቱ አልነበረም፥ እናንተም ራሳችሁ ታውቁታላችሁ። 2ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራንና እንግልትን ብንቀበልም እንኳ፥ በታላቅም ተቃውሞ ፊት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን ድፍረትን አገኘን። 3ምክራችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ከተንኰልም የመነጨ አልነበረምና፤ 4ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። 5እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። 6እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ 7ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ 8ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው።
9ወንድሞች ሆይ! ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሱታላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እየሰበክን በአንዳችሁም ላይ እንኳ ሸክም ላለመሆን ስንል ሌሊትና ቀን እንሠራ ነበር። 10በእናንተ በአማኞች መካከል እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ነበርን እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11አባት ለልጁ እንደሚሆነው እኛም እንዴት ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን እናንተው ታውቁታላችሁ፥ 12በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ እንድትመላለሱ እየመከርናችሁ፥ እያጸናናችሁና እየመሰከርንላችሁ ነበር።
ሁለተኛ ምንባብ
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2 :1-12
ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ
1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ተንኰልን ሁሉ፥ ግብዝነትን፥ ቅንዓትን ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። 2ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ፥ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3እነሆ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችኋልና።
4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፥ 5እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለማቅረብ፥ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፥ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ
“እነሆ፥ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፥ በጽዮን አኖራለሁ፤
በእርሱም የሚያምን አያፍርም፤”
ተብሎ ተጽፎአልና። 7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን
“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”
8 ደግሞም፦
“ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ
የሚጥላቸውም ዓለት ሆነ፤”
የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ አስቀድመውም ለዚህ የተመደቡ ናቸው።
9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። 10ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች መኖር
11ወዳጆች ሆይ! ባዕዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ 12ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር በሚጎበኝበት ቀን፥ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ እርሱን እንድያከብሩት በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።
ወንጌል
የሉቃስ ወንጌል 10:17-24
የሰባው ደቀ መዛሙርት መመለስ
17ሰባዎቹም ሰዎች በደስታ ተመልሰው፦ “ጌታ ሆይ! አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል፤” አሉት። 18ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት። 19እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም ምንም ነገር የለም። 20ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንም ስማችሁ በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
21በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ! መልካም ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። 22ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድንም ማን እንደሆነ ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ አብንም ማን እንደሆነ ከወልድ በቀር ወልድም በፈቃዱ ከሚገልጥለት ሰው በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።”
23ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሳሉ ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፦ “የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው። 24እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙምም።”