August 23 2026

የመጀመሪያ ምንባብ

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3 :1-14

እውነተኛ ጽድቅ

1በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ። ለእናንተ ተመሳሳይ የሆነን ነገር መልሼ ለመጻፍ ለእኔ አይታክተኝም፤ ይህ ለእናንተ ለደኅንነት የሆነ ነውና።

2ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፤ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። 3እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን በእውነትም ከተገረዙት ወገን የሆንን ነንና። 4እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት ነገር ያለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። 5በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 7ነገር ግን ለእኔ ጥቅም የሚያስገኘውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 8አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ ለማወቅ ስል ሁሉ ነገር ጉዳት እንደሆነ አድርጌ እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ነገሮች በማጣት ተጐዳሁ፤ እነርሱንም እንደ ጉድፍ አድርጌ ቈጠርኋቸው፤ በዚህም ክርስቶስን እንዳገኝ፥ 9በክርስቶስም በማመን በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንጂ በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴ ጽድቅ ሳይኖረኝ፥ በእርሱ እንድገኝ ነው፤ 10በሞቱም እርሱን በመምሰል ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል መከራውንም ተካፋይ መሆኔን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ 11ምናልባትም ቢሆንልኝ የሙታን ትንሣኤን እቀዳጃለሁ።

ወደ ግብ ለመድረስ መሮጥ

12እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍጹም ለመሆን አልበቃሁም፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደ ፊት እሮጣለሁ። 13ወንድሞች ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደ ፊት እዘረጋለሁ፤ 14በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያለውን የመጠራት ሽልማት እንዳገኝ ወደ ግቡ እሮጣለሁ። 


ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4:12-19

እንደ ክርስቲያን መከራን መቀበል

12ወዳጆች ሆይ! እንደ እሳት በሚፈትን መከራ ውስጥ ስትገኙ ያልተለመደ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ አድርጋችሁ አትደነቁ። 13ይልቅስ የእርሱ ክብር በሚገለጥበት ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎአችሁ ኀሤት እንድታደርጉ የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በሆናችሁበት መጠን ደስ ይበላችሁ። 14ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ፥ የእግዚአብሔር የክብሩም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። 15ማንም ከእናንተ መካከል እንደ ነፍሰ ገዳይ፥ ወይም እንደ ሌባ፥ ወይም እንደ ክፉ አድራጊ፥ ወይም በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ሆኖ መከራ የሚቀበል አይኑር። 16ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። 17ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአል፤ በቅድሚያም በእኛ የሚጀመር ከሆነ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18እንግዲህ “ጻድቅ እንኳ በጭንቅ የሚድን ከሆነ፥ የዐመፀኛውና የኀጢአተኛው መጨረሻ እንዴት ይሆን?” 19ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።

ወንጌል

ዮሐንስ 15:12-26
12 “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ። 13ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። 14እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። 15ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። 16እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንደሚሰጣችሁ፥ እንድትሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬአችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። 17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዛችኋለሁ።

ዓለም ደቀ መዛሙርትን እንደሚጠላ

18“ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። 19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስላልሆናችሁ ዓለም ይጠላችኋል። 20‘ባርያ ከጌታው አይበልጥም፤’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን ካሳደዱኝ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌንም ከጠበቁ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። 21ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ በስሜ ምክንያት ያደርጉባችኋል። 22እኔ መጥቼ ባልነገራቸው ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ሰበብ የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። 24ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል። 25ነገር ግን በሕጋቸው ‘በከንቱ ጠሉኝ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 26ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ፥ እርሱም ከአብ የሚወጣው የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ 

Previous
Previous

August 30 2026

Next
Next

August 16 2026