September 29 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 1:10-31

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሠተ መለያየት

10ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፣ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ከቀሎዔ ቤተ ሰብ ሰምቻለሁ፤ 12ነገሩም እንዲህ ነው፤ ከእናንተ አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲል፣ ሌላው፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ይላል፤ ደግሞም አንዱ፣ “እኔ የኬፋ ነኝ” ሲል፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔስ የክርስቶስ ነኝ” ይላል።

13ለመሆኑ ክርስቶስ ተከፍሏልን? ጳውሎስስ ለእናንተ ተሰቅሏልን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋልን? 14ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በስተቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 15ስለዚህ በስሜ መጠመቁን የሚናገር ማንም የለም። 16በርግጥ የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰው አጥምቄአለሁ፤ ከእነዚህ ሌላ ግን ማጥመቄ ትዝ አይለኝም። 17ክርስቶስ የላከኝ ወንጌልን እንድሰብክ እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፣ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም።

ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ

18የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ 19እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤

የዐዋቂዎችንም ዕውቀት ከንቱ አደርጋለሁ።”

20ጠቢብ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገምን? 21ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗል። 22መቼም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤ 23እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። 24እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። 25ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል።

26ወንድሞች ሆይ፤ በተጠራችሁ ጊዜ ምን እንደ ነበራችሁ እስቲ አስቡ። በሰው መስፈርት ከእናንተ ብዙዎቻችሁ ዐዋቂዎች አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ኀያላን አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ከትልቅ ቤተ ሰብ አልተወለዳችሁም። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር ብርቱዎችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ። 28እግዚአብሔር የተከበረውን እንደሌለ ለማድረግ፣ በዚህ ዓለም ዝቅ ያለውንና የተናቀውን ነገር፣ ቦታም ያልተሰጠውን ነገር መረጠ፤ 29ይኸውም ማንም ሰው በእርሱ ፊት እንዳይመካ ነው። 30በክርስቶስ ኢየሱስ ለመሆን የበቃችሁት ከእርሱ የተነሣ ነው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችን፣ ቤዛችንም ሆኗል። 31እንግዲህ፣ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ “የሚመካ በጌታ ይመካ።”


ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 4:1-11

ለእግዚአብሔር መኖር

1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቷል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።

7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና፣ ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጕረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ማርቆስ 8:27-38

ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የነበረው ግንዛቤ

27ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

28እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት።

29ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው።

30ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።

ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

31ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።

32እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።

33ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።

34ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35ነፍሱን ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። 36ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? 38በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”

Previous
Previous

October 6 2024

Next
Next

September 22 2024