September 22 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 9:1-15

1ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደ ሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቷል። 3እንግዲህ በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር፣ አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ወንድሞችን ልኬአለሁ። 4ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ያን ያህል በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን። 5ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቅቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።

በልግስና መስጠት

6ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል። 7እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወድዳል። 8ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ 9ይህም፣

“በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል”
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

10ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። 11ሁልጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።

12ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጕድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው። 13የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ስለ ታዘዛችሁና ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ስላሳያችሁት ልግስና ሰዎች ተፈትኖ ስላለፈው አገልግሎታችሁ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ 14ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ይናፍቋችኋል። 15በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።


ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 5:1-9

ለጨካኝ ሀብታሞች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

1እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። 2ሀብታችሁ ሻግቷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። 3ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። 4ልብ በሉ፤ ዕርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የዐጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሷል። 5በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል ኖራችኋል፤ ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። 6እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሓን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም።

በመከራ ውስጥ መታገሥ

7እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። 8እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል። 9ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ፤ ፈራጁ በበር ላይ ቆሟል።

ወንጌል

ማርቆስ 4:24-38

24በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።

የአዳጊው ዘር ምሳሌ

26ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። 27ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ 28ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ 29ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።”

የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ

30ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? 31በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”

33ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። 34ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

35ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። 36እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ። 37በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። 38ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?” አሉት።

Previous
Previous

September 29 2024

Next
Next

September 15 2024