November 12 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 7:7-13
ሕግና ኃጢአት

7 እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? በጭራሽ! ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ ኃጢአትን አላውቅም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ ምኞትን አላውቅም ነበር። 8ኃጢአት ግን በትእዛዝ አማካኝነት አጋጣሚን በመውሰድ ሁሉንም ዓይነት ምኞትን አስነሣ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ የሞተ ነውና። 9እኔም ድሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ። 10እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠው ትእዛዝ ለሞት መሆኑን ተገነዘብሁ፤ 11ኃጢአት በትእዛዝ በኩል አጋጣሚ አግኝቶ አታልሎኛልና፥ በእርሱም ገደለኝ። 12ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፥ ትክክለኛና መልካም ነው።

13እንግዲህ መልካም የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? በጭራሽ! ነገር ግን ኃጢአት ኃጢአትነቱ እንዲታይ፥ መልካም በሆነው ነገር ሞትን ይሠራብኝ ነበር። ይኸውም ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት ያለ ልክ ኃጢአት እንዲሆን ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 1:21-25
21እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሞት ባስነሣው ክብርንም በሰጠው፥ በእግዚአብሔር በእርሱ ትተማመናላችሁ።

22ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ ለወንድማማች እውነተኛ ፍቅር፥ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት በሕያውና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር እንጂ፤ ከሚጠፋ ዘር አይደለም።

24 ምክንያቱም፥

“ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፥

ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነውና፤

ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤

25የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”

የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።

ወንጌል

ማቴዎስ 7:20-29
20ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። 21በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም። 22በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። 23ያንጊዜ ‘ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ’ እላቸዋለሁ።

ቃል ስለሚሰሙና ስለሚፈጽሙ ሰዎች

(ሉቃ. 6፥47-49)

24“ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ጠቢብ ሰውን ይመስላል። 25ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በዓለት ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። 26ይህን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። 27ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።”

28 ኢየሱስ ይህንን ንግግር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ 29እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው።

Previous
Previous

November 19 2023

Next
Next

November 5 2023