November 19 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 5:10-21
10ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ 11ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን።
አዳምና ክርስቶስ
12 ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ፥ ሞትም በኃጢአት በኩል እንደመጣ፥ እንዲሁም ሁሉም ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበረና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም። 14ነገር ግን ለሚመጣው ምሳሌ እንደነበረው እንደ አዳም ሕግን ባልተላለፉት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ።
15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ከሞቱ፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ያለው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት ይበዛ። 16ስጦታውም አንድ ሰው ኃጢአትን በማድረጉ እንዳመጣው ውጤት አይደለም፤ በአንድ በኩል፥ ፍርዱ የአንድን ሰው በደል ተከትሎ ኩነኔን አመጣ፤ በሌላ በኩል ግን ስጦታው ብዙ በደልን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው በደል ምክንያት በዚህ ሰው በኩል ሞት ከነገሠ፥ ይልቁን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ስጦታ የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።
18 እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኩነኔ ለሰው ሁሉ እንደመጣ፥ እንዲሁም በአንድ ሰው የጽድቅ ሥራ ምክንያት ሕይወትን ለማጽደቅ መጣ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። 20በደል እንዲበዛ ሕግ ገባ፤ ነገር ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ጸጋ ይበልጥ በዛ፤ 21ይህም የሆነው፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ሕይወት፥ በጽድቅ በኩል እንዲነግሥ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 2:1-17
1ልጆቼ ሆይ፥ ይህን የምጽፍላችሁ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ብዬ ነው። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኃጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለእኛ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። 3ትእዛዛቱን ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። 4“አውቀዋለሁ” የሚል፥ ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ እርሱ ሐሰተኛ ነው፥ እውነትም በእርሱ ዘንድ የለም። 5ቃሉን የሚጠብቅ ግን በእውነት የእግዚአብሔርን ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን። 6በእርሱ እኖራለሁ የሚል፥ ልክ እርሱ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።
7 ወዳጆቼ ሆይ፥ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍላችሁም፤ ነገር ግን ከመጀመሪያ የነበራችሁ አሮጌ ትእዛዝ ነው እንጂ፤ አሮጌውም ቃል የሰማችሁት ነው። 8በሌላ በኩል አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም በእርሱ እና በእናንተ ዘንድ እውነት ነው፤ ጨለማው አልፏል፥ እውነተኛው ብርሃን እያበራ ነው። 9በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን ግን የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ ውስጥ ነው። 10ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፥ በእርሱም ዘንድ ማሰናከያ የለም። 11ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ይኖራል፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ ጨለማው ዐይኖቹን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።
12ልጆች ሆይ፥ ስለ ስሙ ኃጢአታችሁ ይቅር ስለ ተባለላችሁ እጽፍላችኋለሁ። 13አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። 14ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በውስጣችሁ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ ጽፌላችኋለሁ።
15ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን ነገሮች አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአብ ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፥ የሥጋ ምኞት፥ የዐይን ምኞት፥ በኑሮ ደረጃ መመካት፥ ከዓለም ነው እንጂ ከአብ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል።
ወንጌል
ማቴዎስ 6:5-15
ስለ ጸሎት
5 “ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ በሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡ ና በየመንገዱ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 6አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል።
7 “ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ የሚደጋገሙ ቃላትን አትጠቀሙ፥ እነርሱ ብዙ በመናገራቸው የሚሰሙ ይመስላቸዋልና። 8ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሳትጠይቁት ያውቃልና። 9ስለዚህ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ 10መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን፤ 11የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ 12እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ 13ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’ 14የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ 15ሰዎችን ይቅር ባትሉ ግን፥ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።