November 28 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
ቈላስይስ 1:12-29
12በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። 13እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ 14በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።
ክርስቶስ ከሁሉ በላይ
15እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ 16ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። 17እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው። 18እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። 19እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወዶአልና፤ 20በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ።
21ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በአሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። 22አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤ 23ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።
ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያሳየው ትጋት
24ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ። 25የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት እንዳቀርብላችሁ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ዐደራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ፤ 26ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። 27ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።
28እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን፤ 29እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በእርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 1:13-20
በቅድስና መኖር
13ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። 14ታዛዦች ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። 15ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል።
17ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ የሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። 18ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 19ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። 20እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ።
ወንጌል
ዮሐንስ 5:16-27
ወልድ ሕይወትን ይሰጣል
16አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። 17ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። 18እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።
19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ 20አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። 21ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ 23ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
24“እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። 25እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ 27ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል።