November 21 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 5:10-21
10
የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! 11ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።

ሞት በአዳም፣ ሕይወት በክርስቶስ

12ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። 14ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።

15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! 16ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!

18ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።

20ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ 21ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 2:1-17
1
ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።

3ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። 4“እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ 6ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው። 9በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። 10ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። 11ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

12ልጆች ሆይ፤

ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

13አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

14አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤

ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣

የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣

ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣

ጽፍላችኋለሁ።

ዓለምን አትውደዱ

15ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

ወንጌል

ማቴዎስ 6:5-15
ስለ ጸሎት

5“ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 6አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። 7ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። 8እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።

9“እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤

“ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤

ስምህ ይቀደስ፤

10መንግሥትህ ትምጣ፤

ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣

እንዲሁ በምድር ትሁን።

11የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።

12እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣

በደላችንን ይቅር በለን።

13ወደ ፈተናም አታግባን

ከክፉው አድነን እንጂ፣

መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣

ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን።’

14እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። 15ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

Previous
Previous

November 28 2021

Next
Next

November 14 2021