May 8 2022
የመጀመሪያ ምንባብ
ገላትያ 4:1-12
1እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም። 2አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው። 3እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር። 4ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። 6ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።
7ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ማሰቡ
8እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ 9አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን? 10ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ። 11ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።
12ወንድሞች ሆይ፤ እለምናችኋለሁ፤ እኔ እናንተን እንደ መሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ። እናንተ አንዳች አልበደላችሁኝም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 1:8-12
8እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል፤ 9የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
10ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ 11በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። 12አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ባበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
ሶስተኛ ምንባብ
ሐዋርያት ሥራ 1:12-14
ማትያስ በይሁዳ ምትክ ተመረጠ
12ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ይህም ተራራ ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል ይርቅ ነበር። 13ወደ ከተማዪቱም በገቡ ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፤ እነዚህም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብ፣ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ ቶማስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናኢ የተባለው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ። 14እነዚህ ሁሉ ከሴቶቹና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ጋር እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋር በአንድ ልብ ሆነው ያለ ማቋረጥ ተግተው ይጸልዩ ነበር።
ወንጌል
ሉቃስ 1:39-56
ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች
39ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ 42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና። 45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”
የማርያም መዝሙር
46ማርያምም እንዲህ አለች፤
“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤
47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤
48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና።
ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ
ብፅዕት ይሉኛል፤
49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ
ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤
50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ
እስከ ትውልድ ይኖራል።
51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤
በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤
52ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤
ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤
ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤
54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን
እስራኤልን ረድቶአል፤
55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣
ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።