May 1 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 15:1-19
የክርስቶስ ትንሣኤ

1አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክ ሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ 2የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው።

3እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ 4ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ 5ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ 6ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። 7ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ 8ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቈጠር ለእኔ ደግሞ ታየ።

9እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፣ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ 10ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። 11እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው።

የሙታን ትንሣኤ

12ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? 13የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! 14ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። 15ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ 16ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። 17ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢ አታችሁ አላችሁ ማለት ነው። 18እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። 19ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 1:1-10
የሕይወት ቃል

1ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። 2ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም። በአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤ 3እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአብ፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።

በብርሃን መመላለስ

5ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። 6በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም። 7ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።

8ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። 10ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

ወንጌል

ዮሐንስ 20:19-31
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

19በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 20ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።

21ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። 22ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ 23የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

24በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። 25ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት።

እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ።

26ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 27ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው።

28ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው።

29ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው።

30ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ 31ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

Previous
Previous

May 8 2022

Next
Next

April 23 2022