January 20 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ቲቶ. 3፥ 4 – 7
4ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ 5ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ 6ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ 7ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው። ።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 5:5-12
5ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?
6በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና። 7ስለዚህ ሦስት ምስክሮች አሉት፤ 8እነርሱም መንፈሱ፣ ውሃውና ደሙ ናቸው፤ ሦስቱም ይስማማሉ። 9የሰውን ምስክርነት ከተቀበልን፣ የእግዚአብሔር ምስክርነት ከዚያም ይልቃል፤ ይህ ስለ ልጁ የሰጠው የእግዚአብሔር ምስክርነት ነውና። 10በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። 11ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። 12ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።
ወንጌል
ማቴ. 3፥ 13 -17
የኢየሱስ መጠመቅ
13በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። 14ዮሐንስ ግን፣ “ይህማ አይሆንም፤ እኔ ባንተ መጠመቅ ሲያስፈልገኝ እንዴት አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ተከላከለ።
15ኢየሱስም፣ “ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው፤ ዮሐንስም በነገሩ ተስማማ።
16ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። 17እነሆ፤ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።