January 14 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 11:25-36
እስራኤል ሁሉ ይድናል
25ወንድሞች ሆይ፤ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ፣ ይህን ምስጢር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል በድንዳኔ ውስጥ ዐልፋለች። 26ስለዚህ እስራኤል ሁሉ ይድናሉ፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
“አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤
ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል።
27ኀጢአታቸውንም ሳስወግድ፣
ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳኔ ይህ ነው።”
28እንደ ምሥራቹ ቃል ለእናንተ ሲባል ጠላቶች ናቸው፤ እንደ ምርጫ ከሆነ ግን፣ ለአባቶች ሲባል የተወደዱ ናቸው፤ 29የእግዚአብሔር ስጦታና ጥሪ ጸጸት የለበትም። 30እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ እንደ ነበራችሁ፣ ከእነርሱ አለመታዘዝ የተነሣ አሁን ምሕረት እንዳገኛችሁ ሁሉ፣ 31እግዚአብሔር ለእናንተ ምሕረት ከማድረጉ የተነሣ፣ እነርሱም ምሕረት ያገኙ ዘንድ አሁን የማይታዘዙ ልጆች ሆነዋል፤ 32እግዚአብሔር ለሁሉም ምሕረት ያደርግ ዘንድ ሰውን ሁሉ ባለመታዘዝ ዘግቶታልና።
ውዳሴ
33የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው!
ፍርዱ አይመረመርም፤
ለመንገዱም ፈለግ የለውም!
34“የጌታን ልብ ያወቀ ማነው?
አማካሪውስ የነበረ ማን ነው?”
35“እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣
ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው?”
36ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤
ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 4:1-8
መናፍስትን መርምሩ
1ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 2የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚቀበል መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ 3ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።
4ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል። 5እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ የሚናገሩት እንደ ዓለም ነው፤ ዓለምም ይሰማቸዋል። 6እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።
የእግዚአብሔር ፍቅርና የሰው ፍቅር
7ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። 8የማይወድድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።
ወንጌል
ማቴዎስ 2:1-12
የጠቢባን ከምሥራቅ መምጣት
1በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ 2“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ።
3ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች። 4እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 5እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏልና አሉ፤
6“ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣
ከሌሎቹ የይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤
የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣
ከአንቺ ይወጣልና።’ ”
7ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። 8ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው።
9ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። 10ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። 11ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። 12እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ።