January 29 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ገላትያ 4:1-11
1እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም። 2አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው። 3እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር። 4ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። 6ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።
7ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ማሰቡ
8እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ 9አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን? 10ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ። 11ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።
ሁለተኛ ምንባብ
2 ዮሐንስ 1:1-6
1ሽማግሌው፤
በእውነት ለምወዳት እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤ 2በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፣ 3ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።
4ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው። 6ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።
ወንጌል
ሉቃስ 1:46-56
የማርያም መዝሙር
46ማርያምም እንዲህ አለች፤
“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤
47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤
48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና።
ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ
ብፅዕት ይሉኛል፤
49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ
ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤
50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ
እስከ ትውልድ ይኖራል።
51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤
በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤
52ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤
ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤
ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤
54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን
እስራኤልን ረድቶአል፤
55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣
ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።