February 5 2023

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 1:1-11
1
ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ 2ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞተስፋ ተሰጠ። 3ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ 4በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 5በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። 6እናንተ ራሳችሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩ መካከል ናችሁ።

7በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁ ሁሉ፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ሮምን ለማየት የጳውሎስ ናፍቆት

8ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁም አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። 9ዘወትር ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ 10በጸሎቴ ሁል ጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ።

11እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 1:13-21
በቅድስና መኖር

13ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። 14ታዛዦች ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። 15ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል።

17ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ የሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። 18ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 19ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። 20እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ። 21በእርሱም አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ፤ ስለዚህ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው።

ወንጌል

ሉቃስ 2:36-41
36
ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤ 37ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች። 38በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።

39ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። 40ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።

ኢየሱስ በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ

41ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።

Previous
Previous

February 12 2023

Next
Next

January 29 2023