December 15 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 15:12-32

የሙታን ትንሣኤ

12ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? 13የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! 14ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። 15ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ 16ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። 17ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። 18እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። 19ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።

20ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል። 21ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኗልና። 22ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ 23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። 24ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ 27“ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።

29ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? 30እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? 31ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። 32በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣

“ነገ ስለምንሞት፣

እንብላ፣ እንጠጣ፤”

እንደሚሉት መሆናችን ነው።


ሁለተኛ ምንባብ

2 ጴጥሮስ 3:10-18

10የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል።

11እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ 12ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። 13እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።

14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። 15የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደ ሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ። 16እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፏል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

17እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። 18ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ።

ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን! አሜን።

ወንጌል

ሉቃስ 12:32-40
32 አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።
33 ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤
34 መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
35 ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤
36 እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ
37 ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል።
38 ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው።
39 ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር።
40 እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

Previous
Previous

December 22 2024

Next
Next

December 8 2024