December 8 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 2:1-16
1ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጥላችሁ አልመጣሁም። 2በመካከላችሁ ሳለሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ያውም የተሰቀለውን፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና። 3ወደ እናንተ የመጣሁት በድካምና በፍርሀት፣ እንዲሁም በብዙ መንቀጥቀጥ ነበር። 4ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኀይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባ ባል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ 5ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።
ከመንፈስ የተገኘ ጥበብ
6በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። 7ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው። 8ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር። 9ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣
“ዐይን ያላየውን፣
ጆሮ ያልሰማውን፣
የሰውም ልብ ያላሰበውን፣
እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል፤”
10እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል።
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። 11በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በስተቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። 12ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው። 13እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማር ነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማር ነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው። 14መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ፣ ሊረዳው አይችልም። 15መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
16“ያስተምረው ዘንድ፣
የጌታን ልብ ማን ዐወቀው?”
እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 5:1-5
በእግዚአብሔር ልጅ ማመን
1ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፤ አባትንም የሚወድ ሁሉ ልጁንም እንደዚሁ ይወዳል። 2እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደ ምንወድ በዚህ እናውቃለን፤
3እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፤ 4ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። 5ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?
ወንጌል
ዮሐንስ 9:1-41
ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ
1በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። 2ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት።
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። 4ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ 5በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”
6ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ 7“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት ‘የተላከ’ ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ።
8ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። 9አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ።
ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ።
እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ።
10እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት።
11እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ።
12እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት።
እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ።
ፈሪሳውያን ሰውየው እንዴት እንደ ተፈወሰ ማጣራት ቀጠሉ
13እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። 15ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው።
16ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ።
ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ።
17ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት።
ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ።
18አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስ ጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። 19እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዶአል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው።
20ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ 21አሁን ግን እንዴት ማየት እንደቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” 22ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኲራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። 23ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ።
24ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት።
25እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ” አለ።
26እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት።
27እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ።
28ከዚህ በኋላ በእርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! 29እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።”
30ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። 31እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ 32ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። 33ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።”
34እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም።
መንፈሳዊ ዕውርነት
35ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምታምናለ ህን?” አለው።
36ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው።
37ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው።
38ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም።
39ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ።
40ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት።
41ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።