August 22 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 8:31-39
31ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? 32ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? 33እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ 34ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። 35ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? 36ይህም፣
“ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤
እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን”
ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
37ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። 38ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ 39ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
ሁለተኛ ምንባብ
2 ዮሐንስ 1:1-13
1ሽማግሌው፤
በእውነት ለምወድዳት፣ እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወድዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤ 2በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፤
3ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።
4ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው። 6ይህም ፍቅር፣ በትእዛዞቹ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።
7ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 8እናንተም የደከማችሁበትን ዋጋ እንዳታጡ፣ ነገር ግን ሙሉ ሽልማት እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው። 10ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ 11የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና።
12የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በወረቀትና በቀለም እንዲሆን አልፈልግም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።
13የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።
ወንጌል
ሉቃ. 1:26 – 38
የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ
26በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤ 27የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። 28መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።
29ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ 30መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። 31እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ 33በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”
34ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።
35መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። 36እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ 37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”
38ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ።