August 25 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 1:8-14
ሮምን ለማየት የጳውሎስ ናፍቆት
8ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። 9ዘወትር ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ 10በጸሎቴ ሁልጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ።
11እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። 12ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው። 13ወንድሞች ሆይ፤ በሌሎች አሕዛብ ዘንድ እንደ ሆነልኝ፣ በእናንተም ዘንድ ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ዐቅጄ ሳለሁ፣ እስከ አሁን ድረስ ግን መከልከሌን እንድታውቁ እወድዳለሁ።
14ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ፤
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:8-14
መልካም በማድረግ መከራን መቀበል
8በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። 9ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። 10ስለዚህ፣
“ሕይወትን የሚወድድ፣
መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣
ምላሱን ከክፉ፣
ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።
11ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤
ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤
12ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤
ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤
የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”
13መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? 14ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።”
ወንጌል
ማቴዎስ 27:50-56
50ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ።
51በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ 52መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ 53ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ።
54የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ። 55ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ። 56ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።