April 25 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 9፡11-28
ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ
ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን
የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። የውጭ አካላቸው
ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ
የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር
ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ
ይሆን! ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤
በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና።
ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤ ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውዬው ሲሞት ብቻ
ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ
ያለ ደም የጸና አልነበረም። ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣
ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት
እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም
ረጨው። በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ ደም ሳይፈስ ስርየት
የለምና። እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት በእነዚህ ነገሮች ሊነጹ ግድ ነበር፤ በሰማይ ያሉት ነገሮች ግን
ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ
ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት፣ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ
ገባ። ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ
ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ
መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን
ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል። ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም
ተወስኖበታል። ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ
ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 4:1-11
እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው
መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ
እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ
ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን
ይበቃል። ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ
ይሰድቧችኋል። ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። ወንጌል ለሙታን እንኳ
ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ። የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ
ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ
ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ
መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ
እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም
እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም
ይሁን፤ አሜን።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐንስ 5፡11-30
እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን
ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣
ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣
ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። ሰውየውም የፈወሰው
ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው። አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን
ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። እንግዲህ አይሁድ፣
ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣
ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ
ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ
ያደርጋልና፤ አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር
ያሳየዋል። ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው
ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ
ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን
አብንም አያከብርም። “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤
ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ
ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት
እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ
ሥልጣን ሰጥቶታል። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም
የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤
የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው።
ሥርዓተ ሆሳዕና
1 ቆሮንቶስ 15፡1-8
የክርስቶስ ትንሣኤ
አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክ ሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ
እወዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው።እኔ
የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ
ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም
ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ
በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ
እንደ ጭንጋፍ ለምቈጠር ለእኔ ደግሞ ታየ።
ማቴዎስ 20፡29-34
የሁለት ዐይነ ስውሮች መፈወስ
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። በዚያም ሁለት ዐይነ ስውሮች በመንገድ ዳር
ተቀምጠው ነበር፤ ኢየሱስም በዚያ ማለፉን ሲሰሙ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” በማለት ጮኹ። ሕዝቡም በግሣጼ
ቃል ዝም እንዲሉ ነገሯቸው፤ እነርሱ ግን አምርረው በመጮኽ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” አሉ። ኢየሱስም ቆም ብሎ
ጠራቸውና፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ዐይኖቻችን እንዲያዩ እንፈልጋለን” አሉት።
ኢየሱስም ራራላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሰ፣ ወዲያው አዩ፤ ተከተሉትም።
ማቴዎስ 21፡1-17
ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ
ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ እንዲህ አላቸው “ባቅራቢያችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት
አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው። ማንም ሰው ለምን እንዲህ
ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት፤ ወዲያውኑ ይሰዳቸዋል።” ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ
በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው። “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤ ‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣ በአህያዪቱና
በግልገሏ፣ በውርንጫዪቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው
አደረጉ። 7አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም
ተቀመጠባቸው። ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን፣ በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ
እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ጣል ጣል አደረጉ። ቀድሞት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው ይከተለው የነበረው ሕዝብም
እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፣ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤” “ሆሣዕና በአርያም!”
ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች። ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው
ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ
ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን አባረራቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ
በመገለባበጥ፣ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን፣ ‘የዘራፊዎች ዋሻ’
አደረጋችሁት” አላቸው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም
ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ”
እያሉ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ” አሉት።
ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ
ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” ትቶአቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው አደረ።
ማርቆስ 11፡1-12
ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ
መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ
የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት፤ ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ
ያስፈልገዋል፤ በቶሎም መልሶ ይልከዋል’ ብላችሁ ንገሩት።” እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ እመንገድ ላይ
የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙት፤ ፈቱትም። በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን
ነው?” አሏቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው። ውርንጫውንም ወደ
ኢየሱስ አምጥተው ልብሳቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት። ብዙ ሰዎች ልበሳቸውን በመንገድ
ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 9ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው
የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! የምትመጣው
የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት! ሆሣዕና በአርያም!”። ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ
ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።
በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።
ሉቃስ 19፡28-48
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሞአቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ
ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል
ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ
ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ
ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። 33ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ
አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም
ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ
አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል
ወደ ሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ
እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤ “በጌታ ስም የሚመጣው
ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም
ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም
ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው። ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም
አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሮአል፤ ጠላቶችሽ ዙሪያሽን
ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ
የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላ
ወቅሽምና።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ አስወጣ፤ ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት
ይሆናል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በየቀኑም በቤተ መቅደስ
ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ
ከእርሱ ጋር ተቈራኝተው ትምህርቱን ይከታተሉ ስለ ነበር፣ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።
ዮሐንስ 12፡12-19
በማግሥቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤ 13የዘንባባም
ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ሆሣዕና!” “በጌታ ስም የሚመጣ
ቡሩክ ነው!” “የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!” ኢየሱስም የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ
እንደ ተጻፈ፤ “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤ እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል።” ደቀ መዛሙርቱ
ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለእርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ
በኋላ ነበር። አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ
ነበር። ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ
በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።