April 18 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 7:14-25
ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ። የማደርገውን አላውቅም፤
ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና። ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ
በጎ እንደሆነ እመሰክራለሁ፤ እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት
ነው። በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን
የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም። የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን
ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው። ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ
ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው። ስለዚህ ይህ ሕግ እየሠራ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ ይኸውም
በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ። በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ
ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ
አያለሁ። እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል? በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣
በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 4:18-21
በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው
ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ
ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ
አይችልምና። እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐንስ 3:1-13
ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤
እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣
ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም
ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ
እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ
ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ
አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ
አትገረም፤ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም
አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።” ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤
የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። ስለ ምድራዊው ነገር
ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ
ሰማይ የወጣ ማንም የለም።